ሀገር በአንድነት ትከበራለች፤ በኅብረት ትጠበቃለች።

3
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድነት የጸኑ ሀገራቸውን አስከብረዋል፤ ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀዋል፤ ነጻነታቸውን አጽንተዋል፤ ጥቅማቸውንም አረጋግጠዋል።
ሀገር በአንድነት ትከበራለች፤ በኅብረት ትጠበቃለች። ኢትዮጵያን የነጻነት ቀንዲል አድርጎ ያኖራት፤ በጠላቶቿ ፊት ግርማን የሰጣት፤ የቅኝ ገዢዎች ክንድ ያልበገራት ጊዜያዊ ችግር ያልፈተነው፤ የጠላት ሴራ ያልሸረሸረው አንድነት ስለነበራት ነው።
ዛሬም ይሄው አንድነት ያስከብራታል፤ የቆዬው ኅብረት ያስጠብቃታል። የጠላት ፍላጎት እና ምኞት በበዛበት ቀጣና ያለችው ኢትዮጵያ ከአንድነት ውጭ ምርጫ የላትም።
በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የቀደመ ይዞታዋን የባሕር በር ለማስመለስ፣ በአፍሪካ የነበራትን እና ያላትን ተሰሚነት የበለጠ ለማሳደግ አንድነትን ማጠናከር፣ ለብሔራዊ ጥቅም በኅብረት መቆም ይጠበቅባታል። ስለ ምን ቢሉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን በጠላት የሚመለከቱ፣ መለያየታቸውን የሚሹ ጠላቶች አሉና።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በለጠ ጓንጉል እንዳሉት ኢትዮጵያ ያለችበት መልካምድራዊ አቀማመጥ አስፈላጊ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ አስፈሪ ቀጣና ነው ። በጣም አስፈላጊ እና በጣም አስፈሪ ነው ስንል መልካምድራዊ አቀማመጡ ብዙ አህጉራትን እና ሀገራትን የሚያገናኝ በመኾኑ ነው ይላሉ።
ቀጣናው በወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተመራጭ እና ወሳኝ ነው ይሉታል። የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና (የቀይ ባሕር) እንደ መስቀለኛ መንገድ ብዙዎችን የሚያገናኝ፣ የኀያላንን ቀልብ የሚስብ፣ የብዙ ሀገራት የዲፕሎማሲ መናኾሪያ ነው። ኀያላን ሀገራት ቀጣናውን ለመቆጣጠር የሚሽቀዳደሙበት እና ወታደራዊ ሰፈራቸውን የሚያስቀምጡበት ነው ይላሉ።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጸጋ ብቻ ሳይኾን የመከራም መናኾሪያ ይኾናል፣ ስለ ምን ቢሉ ብዙ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚሽቀዳደሙበት ነውና።
ዓለም በውድድር የተሞላች ናት፤ ውድድሩ ደግሞ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ ሳይኾን ጥሎ በማለፍ የተሞላ ነው፤ በአንደኛው ኪሳራ ሌላው ለማትረፍ ጥረት የሚያደርግበት ነው፤ ስለዚህ ኃያላን ሀገራት በቀጣናው እኔ እቀድም እኔ እቀድም የሚሯሯጡበት፤ የእጅ አዙር ጦርነት የሚጋብዙበት ነው ይላሉ። ያለውን ጸጋ በተረጋጋ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ ለመጠቀም የማያስችል ችግር የሚፈጠርበት አካባቢ እንደኾነም ያነሳሉ።
ኀያላኑ ሀገራት ወደፊትም በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ የማይቀየር ነው፤ ጥቅማቸውን ለማስከበር ምን ያክል አስፈላጊ ቀጣና እንደኾነ ተረድተውታል፤ ስለዚህ ቀጣናውን በቀላሉ ይተውታል ተብሎ አይታሰብም ነው የሚሉት። ቀጣናውን የጉልበት መለካኪያ እንደሚያደርጉትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተሰሚነት ከፍ የሚለው እና ብሔራዊ ጥቅሟም የሚረጋገጠው ይሄን ፈተና በማለፍ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያውያን አንድነትን በማጠናከር ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ነው ያሉት።
የታሪክ ስህተቶችን መሥራት አይገባንም፤ ልዩነትን በውይይት መፍታት፣ ይህ ባይቻል እንኳን ልዩነትን ወደ ጎን በማድረግ የባሕር በር ጉዳይን እንደዋና አጀንዳ መያዝ ይገባል ነው የሚሉት።
የባሕር በር ጉዳይ በጽኑ አቋም መሠራት ያለበት ነው፤ የባሕር በር የፓርቲ ጉዳይ አይደለም፤ የባሕር በር ጉዳይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሲብላላ የነበረ፣ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤ ይህ የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ስለኾነ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት አለብን ይላሉ።
የምሥራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ስበት ኀይል የምትቆጣጠረው ኢትዮጵያ የባሕር በር ካገኘች የበላይነቷን የበለጠ ታጠናክራለች ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኀያል ሀገር ነበረች፤ ናትም፣ የባሕር በር ስታገኝ ደግሞ የበለጠ ተሰሚ እና ገናና ትኾናለች ነው የሚሉት።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢ-ተገማች ነው የሚሉት መምህሩ ነገሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ የበቃ እና የነቃ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ኢ ተገማች የኾነውን እንቅስቃሴ ቀድሞ በመረዳት፣ ለሚመጡ ችግሮች እና ፈተናዎች ቀድሞ በመዘጋጀት እና ወቅቱን የሚመጥን ምላሽ በመስጠት ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የባሕር በርን ማረጋገጥ ከተቻለ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የንግድ ማዕከል እንድትኾን ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል። ቀጣናው እሳት የሚበዛበት ስለኾነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል፤ አጀንዳ ተቀባይ ከመኾን አጀንዳ ሰጭ መኾን ያስፈልጋል፤ አስቀድሞ አጀንዳን በመስጠት የኢትዮጵያን ጥቅም ማሳወቅ ይገባል ነው ያሉት።
በዲፕሎማሲ ቋሚ ፍላጎት እንጂ ቋሚ ጠላትም ኾነ ቋሚ ወዳጅ የለም የሚሉት መምህሩ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አካሄድ ከዚህ በላይ መሄድ አለበት፤ ኢትዮጵያ እንግዶች ሲመጡ እንኳን ደህና መጣችሁ ከሚለው ቀጥሎ የባሕር በርን ጉዳይ ማንሳት ይገባታል ብለዋል።
የባሕር በር ለኢትዮጵያ ምን ያክል አስፈላጊ እንደኾነ በዕውነት እና በመረጃ ተደግፈን መንገር ይገባናል፤ በተለይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ለኾኑ ሀገራት ጉዳዩን በተገቢው መንገድ ማስረዳት ይጠበቃል፤ የባሕር በር እንደ ምግብ እና ውኃ እንደሚያስፈልገን መንገር ያስፈልገናል ነው ያሉት።
ብልሃት የተሞላበት እና ጥንቃቄ ያለበት አካሄድ ከሄድን ሊመጣ የሚችለውን ቀድመን ከተረዳን ጥያቄያችንን ማስመለስ እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንችላለን፤ ለዚህ ደግሞ ለብሔራዊ ጥቅም በኅብረት መቆም እንደሚገባ አስረድተዋል።
ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት ?” በተሰኘው መጽሐፋቸው የአፍሪካ ቀንድ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ መቅሰፍት የሚታመስ እጅግ አደገኛ ከባቢ መኾኑን ጽፈዋል። የጂኦፖለቲካውን ይዘት የሚያተራምስ የጠላት ፍላጎት እና ምኞት እንዳለም ከትበዋል።
ሀገራት በቀይ ባሕር ቀጣና የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ የባሕር በር ከሸቀጥ ማስተላለፊያነቱ በበለጠ ለኢትዮጵያ ሕልውና እና ነፃነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ይላሉ።
በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችዋ፤ በምትገኝበት የጆኦግራፊ አቀማመጥዋ፣ በፖለቲካ ይዞታዋ፣ በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት እና በታሪክ ምክንያት ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር እንድትፈርስ የሚፈልጉ እና ለዚህም ሌት ከቀን የሚሠሩ ጠላቶች አሏት ነው የሚሉት። ኢትዮጵያ ራሷን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችላት ከጠላቶችዋ ጋር የሚመጣጠን ትጥቅ እና ኀይል ማዘጋጅትም አለባት ይላሉ።
በቀይ ባሕር በኩል በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሕልውና ወሳኝ መኾኑን የሚያሳይ ነው፤ ኢትዮጵያ በአንድ ወይንም በሌላ መንገድ አሰብ ካልተመለሰላት ችግሩ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተላለፈ ይኖራል እንጂ ዝም ብሎ የሚታይ አይደለም ይላሉ።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የዚህ ዘመን ትውልድ በመግባባት እና በአንድነት መጽናት ይጠበቅበታል፤ እንደዛ ከኾነ የገናናዋን ሀገር ታሪክ ክብር ያስጠብቃል፤ የቀደመ ጥቅሟንም ያስከብራል ብለዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት ደንበኞቹን እየጠበቀ ነው።