የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት ደንበኞቹን እየጠበቀ ነው።

5
ባሕርዳር፡ ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መነሻው ሕዝቡ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዲያገኝ ለማስቻል የተዘረጋ አሠራር ነው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኞችና ሙያተኞች ይህንን የአማራ ክልል የአንድ ማዕከል የመሶብ አገለግሎት ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የተገኙ ጋዜጠኞች ማዕከሉን በመጎብኘታቸው ለዘገባ የሚኾኑ መነሻ ሀሳቦች እንዲያገኙ ማድረጉን አንስተዋል።
በርካታ ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚያገኘው ታች ላይ ባሉ የሥራ መዋቅሮች ስለኾነ ከክልሉ ከተማ እና ሜትሮፖሊታንት ከተሞች ባሻገር አገልግሎት መስጫ ማዕከሉ እስከ ታች ድረስ እንዲስፋፋ ጠይቀዋል።
የክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ያልገቡ ተቋማትም ወደ ማዕከሉ በመግባት ለተገልጋዮች ተገቢ እና ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ አስተያየት ሰጥተዋል።
በቀጣይም የማኅበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘገባዎችን በመሥራት ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አሥተባባሪ ተማረ አቤ የክልሉ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን የፈተሸበት ኹኔታ የሕዝቡን እሮሮ ሊፈታ የሚችል መኾኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በክልሉ ጅማሮውን ቢያደርግም በክልሉ የሚገኙ ስምንት ሜትሮፖሊታንት ከተሞች ላይ ለማስጀመር እየተሠራ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዋና አገልግሎቶችን ሰብሰብ አድርጎ ለመስጠት የተቋቋመ ተቋም መኾኑን ተናግረዋል። አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ፣ ፈጣን እና ዘመናዊ ለማድረግ መንግሥት ከነደፋቸው ሪፎርሞች ውስጥ አንዱ ነውም ብለዋል።
አሁን ላይ ቁጥራቸው 10 የክልል እና አራት የፌደራል ተጠሪ ተቋማት ወደ ማዕከሉ በመግባት ተገልጋዮችን በፍጥነት እና የሥራ ጥራት ለማገልገል ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።
የሥራ እና ክህሎት፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት፣ የመሬት፣ የገቢዎች፣ የማዕድን ሀብት፣ የትምህርት፣ የፍትሕ፣ የኢሚግሬሽን፣ የፖስታ አገልግሎት፣ የከተማ ልማት፣ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ፣ የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ፣ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ለሁሉ አገልግሎቶች ሥራ የጀመሩ ተቋማት መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ተቋማቱ ወደ አገልግሎቱ ሲገቡ ጥናት የተደርገባቸው ብልሹ አሠራር፣ ቅሬታ እና አቤቱታ የሚበዛባቸው፣ ተገልጋዮችን ለእንግልት ይዳርጋሉ ተብለው የሚታሰቡ ዘርፎች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የታገዘ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት የተደራጀ መኾኑንም ገልጸዋል። በአካልና በበይነ መረብ (ኦንላይን) አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ተገልጋዮች ተገቢ እና ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እና አለማግኘታቸው እየተገመገመ አስተያየት እና ጥቆማዎች የሚቀበሉበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።
ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ባለመሠራታቸው ግን በሚፈለገው ልክ ተገልጋዮች እየተገለገሉ እንዳልኾነ ነው የጠቀሱት። ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮም ባለፉት ሁለት ወራት በሚጠበቀው ልክ ባይኾንም ከ5 ሺህ በላይ ደንበኞች በማዕከሉ ተገልግለዋል ብለዋል።
በቀጣይ አገልግሎቶችን ሰብሰብ በማድረግ እና ተራማጅ የኾነ ሀሳብ በመያዝ ተራማጅ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እስከ ወረዳ ድረስ ለመመስረት እና አገልግሎት ለመስጠት እንደታሰበ ተናግረዋል። ከክልል አልፎ ለሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ መቀመሪያ እንዲኾንም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሁሉ አገልግሎት ባለሙያ ታድሷል አዳነ በርካታ ተገልጋዮች ወደ ማዕከሉ አገልግሎቶችን ፈልገው ሲመጡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን አውቀው እንደሚመጡ መታዘባቸውን ተናግረዋል።
ጥቂቶች ደግሞ ሁሉንም አገልግሎቶች ማግኘት እየቻሉ በግንዛቤ አለመኖር ከፊሎቹን የተለያዩ ተቋማት ላይ አጠናቀው እንደሚመጡ አንስተዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ሃና ታደሰ ወደ ማዕከሉ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ተገልጋዮችን በትህትና ተቀብላ አገልግሎት ወደ ሚፈልጉት የሥራ ክፍል የማገናኘት ሥራዎችን እንደምትሠራ ነግራናለች።
ወይዘሮ ይርበብ ፈጠነ ደግሞ በአማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ተገልጋይ ናቸው። ከአዴት አካባቢ እንደመጡ የነገሩን ተገልጋይዋ በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እንደሚያገኙ ባለመረዳት ከማዕከሉ ውጭ ባሉ ሁለት ተቋማት ከአንዱ ወደ ሌላው ተቋም በመሄድ ውጣ ውረዶች እንደገጠሟቸው ነግረውናል።
ወደ አማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል ከሄዱ በኋላ ግን ፈጣን አገልግሎት ማግኘታቸውን ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ለ84 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የቤት መሥሪያ ትክ ቦታ አስረከበ።
Next articleሀገር በአንድነት ትከበራለች፤ በኅብረት ትጠበቃለች።