እንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ለ84 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የቤት መሥሪያ ትክ ቦታ አስረከበ።

3
እንጅባራ: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መሬት የተረከቡ አርሶ አደሮች በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ማስፋፊያ ግንባታ ምክንያት በ2010 ዓ.ም ከይዞታቸው የተነሱ እና በወቅቱ ትክ ቦታ ያልተሰጣቸው እንደነበር ተገልጿል።
መሬት የተረከቡ አርሶ አደሮችም የመንግሥትን የልማት አጀንዳ በመደገፍ መሬታቸውን በቅንነት ከለቀቁ ረጅም ዓመታትን ቢያስቆጥሩም በወቅቱ ትክ መሬት ባለመሰጠቱ ለእንግልት ተዳርገው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ዘግይቶም ቢኾን የረጅም ዓመታት ጥያቄያቸው ዛሬ ላይ ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ነው የገለጹት።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የቆዬ ጥላሁን ትክ ቦታ የተሰጣቸው አርሶ አደሮች ለእንጅባራ ከተማ ልማት የጎላ ድርሻ የነበራቸው መኾናቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የዛሬዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የቆዬ የ126 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የትክ መሬት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ተደርጓል ነው ያሉት።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክንዴ ብርሃን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ካሣ በወቅቱ ቢከፍልም ከተማ አሥተዳደሩ ትክ ቦታ ማዘጋጀት ባለመቻሉ የመሬት ርክክቡ መዘግየቱን ተናግረዋል።
ለትክ መሬት ሲባል ለተነሱ አርሶ አደሮች ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ካሣ መክፈሉንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት የመንግሥት ቁልፍ አጀንዳ መኾኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ ምላሽ የተሰጣቸው አርሶ አደሮችም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬታቸውን ለቀው በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ዓመታት ሲጉላሉ የነበሩ እንደኾነ አንስተዋል።
በየደረጃው ያሉ የሥራ ኀላፊዎች ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሚፈጠረውን እንግልት መቀነስ እና መንግሥትን ከተጨማሪ ወጪ መታደግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበክልሉ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ላይ የተሠማሩ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሉ።
Next articleየአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት ደንበኞቹን እየጠበቀ ነው።