በክልሉ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ላይ የተሠማሩ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሉ።

4
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ ከኾኑ እና ሰዎች ገንዘብን ብቻ አልመው ከሚከውኗቸው ወንጀሎች መካከል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አንዱ እና ቀዳሚው ነው፡፡
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለብዝበዛ ዓላማ ሰዎችን በተለይም ሴቶች እና ሕጻናትን በኃይል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ማለት ነው፡፡
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በተደራጀ አደገኛ ሰንሰለት የሚመራ ነው፡፡ ከከተማ እስከ ገጠር በስውር እና በድብቅ የሚሠሩ ወኪሎች እንዳሏቸውም ይነገራል።
ብዙዎቹ ከሀገር የሚወጡት ይህንን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚመሩት እና የሚያደራጁት ደላላዎች በሚያወጡት ፕሮግራም መሠረት መኾኑንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
አሁን አሁን የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት በቀላሉ እንደሚልኩ የሚያመላክቱ ማስታወቂያዎች በብዛት ሢሠራጩም እየተስተዋለ ነው።
ሕጋዊ በኾነ ፈቃድ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሥራ ላይ የተሠማሩ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሉ ያሉት በሥራ እና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት እና የሥራ መረጃ ዳይሬክተሩ ጌታሰው መንጌ ናቸው፡፡
እነዚህ በክልሉ እውቅና እና ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች ወደ 38 የሚጠጉ እንደኾኑም ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም በክልሉ ያለ ዜጋ ወደ ውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመሰማራት ሲፈልግ መመዝገብ እና መመልመል ይችላል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች በአዋጅ ቁጥር 13/89 በወጣው አዲስ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ደንብ ለምዝገባም ኾነ ለምልመላ ዜጎችን ምንም አይነት ክፍያ አያስከፍሉም ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በፊት ለምርመራ በሠራተኛ የሚሸፈን የነበረውን ወጭ አዋጁ በአሠሪዎች እንደሚከፈልም ይደነግጋል ነው ያሉት፡፡ ዜጎች ይህንን በመረዳት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ ማስታወቂያዎችን በማየት እና በየአካባቢው ባሉ ሕገ ወጥ ደላሎች ያለ አግባብ ብዝበዛ መዳረግ የለባቸውም ብለዋል፡፡
ሕጋዊ የኾነውን መንገድ መከተል እንዳለባቸውም በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሰዎች ዝውውር ወይም በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ ለሚደርጉ አካላት በኬላዎች እና በድንበሮች ላይ ቁጥጥር እያደረገ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የባሕር ዳር ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስማረ ጫኔ ናቸው፡፡
በኤርፖርቶች ላይም ትክክለኛ ሰነድ መያዛቸውን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡
የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊ ብዛት ያላቸው ዜጎች ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ይመጣሉ ያሉት ኀላፊው ያንን አጋጣሚ በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር መውጣት አላስፈላጊ ገንዘብ ከመበዝበዝ ጀምሮ ሕይዎትን እስከ ማሳጣት የሚያደርስ መኾኑን የማስገንዘብ ሥራ በሰፊው ይተገበራልም ነው ያሉት፡፡
ዜጎች በቅርበት ፓስፖርት በሕጋዊ መንገድ ማግኘት ከቻሉ በሕገ ወጥ መንገድ ያለውን አማራጭ ከመውሰድ ይቆጠባሉ ብለዋል። “በቅርቡ የኢሚግሬሽን አገልግሎት በወልድያ፣ በጎንደር እና በደብረ ብርሃን እንደሚጀመርም” ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በምንም አይነት መንገድ በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል የለበትም፤ ሀሰተኛ ሰነድ የሚሰጥ አካል ካለም መጠቆም ወይም ማስያዝ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ጥያቄም ካላቸው የጽሕፈት ቤቱን ድረ ገጽ መመልከት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ነጻ የስልክ መስመር 8133 በመደወል አስፈላጊ መረጃዎችን መጠየቅ ይቻላል ብለዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ከዚህ በፊት የነበረውን አሠራር በማዘመን ፓስፖርት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማውጣት ይወስድ የነበረውን ጊዜ እና እንግልት ለመቀነስ ከሰው ኃይል ጀምሮ አጠቃላይ የሪፎርም ሥራ መሥራቱንም አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
Previous article“የኢትዮጵያ እና ማሌዢያ ግንኙነት ከንግድ ባለፈ ትርጉም ወዳለው ትብብር ተሸጋግሯል” ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ 
Next articleእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ለ84 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የቤት መሥሪያ ትክ ቦታ አስረከበ።