
አዲስ አበባ: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማሊዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሒም በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው። በኢትዮ ማሊዥያ ከፍተኛ ፎረም ላይ ስለ ኢትዮጵያ ዕድገት ሃሳብ አንጸባርቀዋል።
የኢትዮጵያ እና የማሊዥያ ግንኑነት ጥልቅ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ማሊዥያ ኢትዮጵያን የምትገነዘባት ሰብዓዊነት ያላት፣ ለሰላም እና ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የምትሰጥ ሀገር አድርጋ ነው ብለዋል።
ያኔ ነብዩ መሐመድ የቁረሽ ቤተሰብን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ ሀገሩ ፍትሕ እና ሰላም ያለበት በመኾኑ እንደኾነም ገልጸዋል። እሱን ከንጉስ ነጃሺ ተምረናል፤ ኢትዮጵያ ስንመጣ እና ሐበሻ ሀገር ስንኾን ሰላም የሚሰማንም ለዚህ ነው ብለዋል።
ምዕራባውያኑ የሠለጠኑት በቴክኖሎጂ አደጉ፤ ቀጥለውም ቀኝ ግዛት ያዙ፤ ቀኝ ግዛት የሥልጣኔ መገለጫ ነው ወይ? የሚለው አሁን ያጠያይቃል ነው ያሉት። ሰብዓዊነት ላይ ግን ይቀራቸዋል ብለዋል።
ማሊዥያ በዓለም በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በአፍሪካ፤ ስለዚህ አብረን እንድንሠራ የሚያግዙ ብዙ ምክንያቶች አሉን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በከተማ ማዘመን፣ በኃይል ግንባታ እና በመሠረተ ልማት እየሠራች ያለችው ሥራ በጣም የሚበረታታ ነው ብለዋል። ብዙ ለውጦች እንዳሉም ገልጸዋል።
ማሊዥያውያን ባለሃብቶችም በሰሚ ኮንዳክተር፣ በአይሲቲ፣ በድጅታል፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በምግብ ነክ ዘርፎች እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
