
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሥልጣኔውን በባሕር በር ያረቀቀ፣ ሉዓላዊነቱን በባሕር ኀይል ያስጠበቀ ጥንታዊ ሕዝብ የባሕር በር ምን እንደኾነ ጠንቅቆ ያውቃል።
ኢትዮጵያ የሥልጣኔዋን ሐውልት ከፍ አድርጋ ያቆመችው፣ የታላቅነቷን ዝና ለዓለም ያሳየችው፤ ከጥንት ጀምሮ ከዓለም ሀገራት ጋር ግንኙነት የጀመረችው፤ ንግድን ያቀጣጠለችው፣ በዓለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መድረክ የራሷን ደማቅ አሻራ ያስቀመጠችው በባሕር ነበር።
የኢትዮጵያ መርከቦች በቀይ ባሕር እና በሌሎች ውቅያኖሶች እንደ አሻቸው ተመላልሰዋል፤ ከኢትዮጵያ ያለውን ጸጋ ለዓለም አድርሰዋል፤ በሌላው ዓለም ያለውንም ወደ ኢትዮጵያ አምጥተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ጀግኖች የኢትዮጵያን የባሕር ክልል እና ክብር ሲያስጠብቁ ኖረዋል። ከዚያም እየተሻገሩ የቀጣናውን ሰላም አስከብረዋል።
የኢትዮጵያን እርዳታ ለጠየቁ እና ከባሕር ማዶ ላሉ ወገኖችም በባሕራቸው አማካኝነት ደርሰዋል። ከጭንቅም ታድገዋል።
ታዲያ በባሕር ላይ ገናና ታሪክ እና ስም ያላት ኢትዮጵያ ከፊት እና ከኋላ፣ ከግራ እና ከቀኝ በሚያዋክቡ ጠላቶች፣ ወቅቱን እና የመጻዒውን ዘመን ባልተረዱ ቡድኖች ምክንያት የባሕር ክልሏን እና የባሕር በሯን ካጣች የአንድ ትውልድ ዕድሜ ተቆጥሯል።
የባሕር በር ይገባኛል ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ጠፍቶ አያውቅም። ሁሉም በውስጡ ሲያስበው እና ጊዜ ሲጠብቅ ኖሯል። ነገር ግን የባሕር በርን ጉዳይ ያነሱ እንደ ክፉ አድራጊ ይቆጠሩ ነበር። ዛሬ ጊዜው ደርሶ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የነበረው ጥያቄ አደባባይ ወጥቷል።
በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በለጠ ጓንጉል ኢትዮጵያ በተሳሳተ የፖለቲካ ስሌቶች እና የፖለቲካ ሽፍጦች ባለፉት ዓመታት ከቀይ ባሕር ጥቅም ተቋዳሽ ሳትኾን ቆይታለች ይላሉ።
ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ጠላቶች ትኩረት የሚያደርጉት በቀይ ባሕር በኩል ነው የሚሉት መምህሩ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሱ የውጭ ጠላቶች ሁሉ የቅድሚያ ትኩረታቸው ቀይ ባሕር እንደኾነ ነው የሚያነሱት።
በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ባሕረ ነጋሽ የሚባለው አካባቢ ከፍተኛ ጠላት የሚበዛበት እንደኾነ እና የኢትዮጵያ ነገሥታትም የሀገርን ጥቅም ለማስከበር ታላቅ ተጋድሎ ሲያደርጉ መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
“ቀይ ባሕር ከቀይ ደም የበለጠ ነው” የሚሉት መምህሩ የባሕር በር በጣም አስፈላጊ ነው፤ በዓለም ተሞክሮ ውስጥ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ሃብታም ቢኾኑ እንኳን ኀያል መኾን አይችሉም፤ ባሕር ከሌለ የሀገር ምስጢር ተላልፎ ይሰጣል፤ ባሕር ከሌላ ከሌሎች ጥገኛ ለመኾን ግዴታ ይኾናል ነው የሚሉት።
የባሕር በር አለመኖር ማለት ቤት ሠርተህ መውጫ መግቢያ መንገድ አለማግኘት ማለት ነው፤ ከቤት ውስጥ ብቻ መኖር አይቻልም፤ መውጫ እና መግቢያ ያስፈልጋል፤ የባሕር ጉዳይ ለሀገራት እጅግ ወሳኝ እና አስፈላጊ ጉዳይ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የነበራት፤ በባሕር በር ስትጠቀም የኖረች ናት፤ ነገር ግን በተፈጠረው ጫና እና በተፈጠረው የፖለቲካ ስህተት ባሕር አልባ እና የተዘጋች ሀገር ኾናለች ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ የዘገየ እና ያረፈደ እንጂ ለምን ተነሳ የሚባል አይደለም፤ ከመቅረት ማርፈድ ይሻላል እንዲሉ ጥያቄው አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በባሕር በር ጥያቄ የጋራ መግባባት መያዝ ያስፈልገዋል የሚሉት መምህሩ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት፣ በታሪክ፣ በሕግ እና በመልካ ምድር የሚገባት እንደኾነ መግባባት ያስፈልጋል ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የዋዛ አይደለም፤ የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው፤ ኤርትራ እና ሌሎች ኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካዋን ለማርገብ ያነሳችው ጥያቄ ነው እንደሚሉት ሳይኾን የኢትዮጵያ ጥያቄ የትውልድ እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው ይላሉ።
መንግሥት ይመጣል ይሄዳል፤ ሕዝብ እና ሀገር ግን ቀጣይ ናቸው፤ ሀገር ቋሚ ናት፤ የባሕር በር ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነው ይሉታል።
ባለፉት ዓመታት የባሕር በር ጉዳይ እንዳይነሳ ሲደረግ ኖሯል፤ ጥያቄውን የሚያነሱ አካላትም እንዲሸማቀቁ ሲደረግ ኖሯል፤ አሁን ላይ የባሕር በር ጉዳይ መነሳቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የባሕር በር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም፤ ይህ የሕዝብ አጀንዳ ብሔራዊ ጥቅም ነው ይላሉ።
የባሕር በር ጉዳይ የተዘጋ ዶሴ ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ አይመለከታትም የሚለው እሳቤ ትክክል ያልኾነ እና ውኃ የማያነሳ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ኾና በኖረችባቸው ዓመታት የፈለገችውን ሳታደርግ፣ የሌሎች ሀገራትን በጎ ፈቃድ ስትጠይቅ ኖራለች፤ በምጣኔ ሃብት እና በማኅበራዊ ጉዳትም ስትጎዳ ኖራለች ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለኢትዮጵያ መቼም አይተኙላትም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ ጥረታቸውን መቀጠላቸው የማይቀር ነው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከጎረቤት ሀገራት እስከ ኀያላን የዓለም ሀገራት የማይፈልጉት ጉዳይ ነው፤ ይህ መታወቅ ያለበት ነው ይላሉ።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሕዳሴ ግድብ አሸንፈን አንደኛውን ብሔራዊ ጥቅም አሳክተናል፤ አሁንም ሌላኛውን ብሔራዊ ጥቅም ለማሳካት የሚፈትኑንን ማሸነፍ አለብን ነው የሚሉት።
በዲፕሎማሲ ነጻ ምሳ የሚባል ነገር የለም፤ ነጻ ምሳ ከሌለ ደግሞ መክፈል አለብህ፣ ስለዚህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና የሚገባትን ለማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ማጠናከር አለባት ይላሉ።
“ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ ብሔራዊ አቅሟን ማሳደግ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው፤ ብሔራዊ ጥቅም ያለ ብሔራዊ አቅም አይሳካም” ነው የሚሉት።
የዲፕሎማሲ አቅምን በማሳደግ አጀንዳችንን ለዓለሙ ማኅበረሰብ ማድረስ አለብን፤ ኢትዮጵያ ሌሎች ባይቀበሉትም የዲፕሎማሲ እና የሰላም አማራጮችን ማስቀደም አለባት፤ የዲፕሎማሲ አማራጭ ሲያድግ ዓለም ያየናል፤ ይረዳናል ነው ያሉት።
ብሔራዊ አንድነት መፍጠር ሌላው ጉዳይ መኾኑን ነው ያነሱት። በጉዳዩ ላይ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር አጀንዳችንን ማስረጽ አለብን፤ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በሥነ ልቦና፣ በሕግ እና በመልካ ምድር እንደሚገባት ማስረዳት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።
የሕዳሴ ግድብ መሳካት ለባሕር በርም መነሳሻ ይኾናል፤ ነገር ግን በጥንቃቄ መመራት አለበት፤ በዓባይ ጉዳይ የጆግራፊ የበላይነት ስለነበረን ነው በቀላሉ ማሳካት የተቻለው፤ እኛ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ስለኾንን ማሳካት ተችሏል፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ ግን ከዓባይ የተለየ ነው፤ አሁን ላይ ሃብቱ እጃችን ላይ የለም፤ ብዙ ተዋንያንም አሉበት፤ ስለዚህ ከዓባይ በተሻለ ጉልበትን በመጨመር፣ የዲፕሎማሲ አቅምን በማሳደግ የባሕር በር ጉዳይን ማሳካት ያስፈልጋል ነው የሚሉት።
የባሕር ጉዳይ የሁላችንም አጀንዳ፣ የሁላችንም ጥያቄ፣ የሀገር ጥቅም መኾኑን መረዳት አለብን፤ የባሕር በር ጉዳይ ለአንድ ወገን ብቻ የሚሰጥ አይደለም፤ ለሁላችንም የሚያስፈልግ፣ የሁላችንም ነው እንጂ ብለዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
