በአዕምሮ እና በአካል የጠነከረ ትውልድን ለመገንባት የሕፃናትን መብቶች ማክበር ይገባል።

3

ጎንደር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕጻናት ጥበቃና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት የጎንደር ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በዓለም ለ36ኛ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሕጻናት ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል።

 

ሕፃናት ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በጤናቸው እና በደኅንነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።

 

ሕፃናት ያለመገደድ፣ በአካላቸው ከጭካኔ እና ኢ-ሰብአዊ ከኾነ ቅጣት ነጻ የመኾን መብቶች አሏቸው።

 

በመድረኩ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የከንቲባው ማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ አወቀ ተፈራ የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ ሕፃናትን ከጉዳት መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ማገዝ የሚቻልበትን ኹኔታ ለማመቻቸት ነው ብለዋል።

 

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ትግስት ገዳሙ በበኩላቸው በዓለም ለ36ኛ እና በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ”የሕጻናት ጥበቃና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕፃናት” በሚል ሃሳብ በዓሉ መከበሩ በከተማ አሥተዳደሩ የሕጻናት ጥቃቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ለመከላከል እንደኾነ ጠቅሰዋል።

 

በአዕምሮ እና በአካል የጠነከረ ትውልድን ለመገንባት የሕፃናትን መብቶች ማክበር እንደሚገባ ተወካይ ኀላፊዋ ተናግረዋል።

 

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሕፃናት ፖርላማ ኀላፊ ሕጻን ልዕልተወይን አዕምሮ አሁን ላይ በሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየተበራከተ መምጣቱን ጠቅሳለች።

 

በመኾኑም ለሕፃናት ጥበቃ ሁሉም ኀላፊነቱን በመወጣት ከጎናችን ሁኑ በማለት መልዕክት አስተላልፋለች።

 

ወላጅ ወይዘሮ ሰዓዳ ለገሰ በበኩላቸው ሕፃናት አድገው ነገ ለሀገራቸው እንዲጠቅሙ አሥተዳደጋቸው ላይ መሥራት የወላጅ፣ የመምህራን፣ የመንግሥት እና የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት ነው ያሉት።

 

ሕፃናትን ትምህርት ቤት ስንልክ ከእውቀት ባለፈ በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲኾኑ አድርጎ መቅረጽ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 

በመድረኩም ሕፃናትን በጉዲፈቻ የሚያሳድጉ ወላጆች የልጆች ርክክብ፣ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ለምግብ ፍጆታ የሚውል ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

 

ዘጋቢ:- ማኅደር አድማሴ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሮዝመሪ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን የስልጤ ዞን ገለጸ።
Next articleለብሔራዊ ጥቅም፣ ብሔራዊ አቅም መፍጠር ይገባል።