
ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አለባቸው እና ማስተዋል የልብስ ስፌት እና ሹራብ ሥራ የኅብረት ሽርክና ማኅበር በባሕር ዳር ከተማ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ሥራዎች ኢንተርፕራይዝነት ተጀምሮ ወደ መካከለኛ ኢንቨስትመንት አድጓል።
ማኅበሩ ሲጀመር ቢሮክራሲ እንዳላጋጠመው እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደተደረገለት የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ ይርጋ አይቸው ናቸው። ድርጅቱ ለ429 ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
አቶ ይርጋ ድርጅታቸው በአቅሙ ለማምረት እና ከተኪ ምርት ወደ ኤክስፖርት አምራችነት ለማደግ የኃይል አቅርቦት ችግር መኖሩን ተናግረዋል።
ሌሎች የመሠረተ ልማት እጥረቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። በምርት ጥራት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አሰፋ ወረታ (ዶ.ር) በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያሉትን ምቹ ሁኔታ እና ማነቆዎችን አንስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የክልሉ ኢንቨስትመንት የተቀዛቀዘ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ የክልሉ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለመተግበር ማገዝ ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
በጸጥታ ችግር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የኢንቨስትመንት ተቋማት የውድመት ዒላማ መኾናቸው እና ለኢንቨስትመንት ተቋማት ይደረግ የነበረው ጥበቃ መቅረቱም የዘርፉ ችግር መኾኑን ነው የገለጹት።
ውስብስብ ቢሮክራሲ ሌላኛው ማነቆ እንደኾነም ዶክተር አሰፋ ተናግረዋል፡፡ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማነስ እና የኃይል መቆራረጥም ኢንዱስትሪዎች በአቅማቸው እንዳያመርቱ እና እንዲከስሩም አድርጓቸዋል ነው ያሉት፡፡
የኢንቨስትመንት ፖሊሲው ቶሎ ቶሎ መቀያየር፣ የዋጋ ግሽበት፣ ለኢንዱስትሪው የሚመጥን የተማረ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የመሬት አቅርቦቱ ከሦስተኛ ወገን አለመጽዳት፣ ደካማ የግሉ ዘርፍ መዋቅር የዘረዘሯቸው ችግሮች ናቸው።
የአልሚዎች ቦታን አጥሮ ማስቀመጥ፣ በፕሮጀክት ዕቅዱ ልክ ሥራ አለመጀመር፣ የተማረ የሰው ኃይል አለመቅጠር እና በቂ ክፍያ አለመክፈል ውስንነቶች የሚታዩት ከመጀመሪያውም እውነተኛው አልሚ መኾኑ ሳይረጋገጥ ቦታ ስለሚሰጥ ነው ይላሉ ዶክተሩ።
ባለሃብቶች አስተማማኝ ዋስትና ስለማያገኙ ከፍተኛ ገንዘብ እና የሰው ኃይል በሚጠይቁ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሠማራት እንደሚፈሩ የገለጹት ዶክተር አሰፋ እሴት በማይጨምሩ አነስተኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሠማራት ይገደዳሉ ብለዋል፡፡
ተቀራርቦ መወያየት እና መሥራትንም በመፍትሔነት ጠቅሰዋል፡፡ ለኢንቨስትመንት መጠናከር የንግድ ምክር ቤቶችን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ተቀዛቅዞ የነበረውን የክልሉ ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት አየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ “ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ማነቆዎች እየተፈቱ ነውም ብለዋል፡፡ በዚህም በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ላይ “የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ46 ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉንም” ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ አለመረጋጋት ቢኖርም ኢንቨስትመንቱ ላይ የጎላ ጥፋት አለማድረሱን እና ይህም የኢንቨስተሩን ስጋት እንደሚቀንስ አቶ እንድሪስ ገልጸዋል፡፡
እንደ ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የዲጂታላይዜሽን የአሠራር ማዕቀፎች ለምርታማነት እና ቅልጥፍና መሠራቱንም ኀላፊው ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ መዘግየት፣ የምርታማነት ችግር፣ መሬት አጥሮ ማስቀመጥ እና ላልተፈለገ ዓላማ መጠቀም፣ የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት በዘርፉ ችግርነት መጠናታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
መሬት ከወሰዱ እና አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ልማት የማይገቡ ባለሃብቶችን ለማስተካከል ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
መንጠቅ ግብ ባይኾንም እርምጃ መውሰድ በማስፈለጉ በ2017 በጀት ዓመት 986 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተነጥቀዋል ብለዋል። 893 ሄክታር መሬትም ወደ መሬት ባንክ መመለሱን ገልጸዋል።
የተፈጠረው የሥራ ዕድል በሚፈለገው ልክ ባይኾንም በ2017 በጀት ዓመትም ለ64 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
