ዜጎች በስደት ሕይወታቸው ለሚገጥማቸው ማንኛውም የጤና እክል መፍትሄ የሚሰጥ ፕሮጀክት ይፋ ኾነ።

3

አዲስ አበባ: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስደት በዜጎች ሕይወት ላይ እና በሀገር ገጽታ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከባድ እየኾነ መጥቷል። በተለይም ዜጎች በስደት ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው የጤና እክሎች ምክንያት ለበርካታ የአካል እና የሥነልቦና ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ።

 

ችግሩን በማጤን እና መፍትሄ በመፈለግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባባሪ አካላት ጋር በመኾን ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል የኢኖቬት ፕሮጄክት ማስጀመሪያ መርሐግብርን ይፋ አድርጓል።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኖቬት ፕሮጀክት ዋና ኀላፊ ካሳሁን ሃብታሙ (ዶ.ር) እንዳሉት የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና የሥልጠና ተቋማት በስደተኛ የቤት ሠራተኞች ጤና ላይ ለሚደርስ እክል ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

 

ፕሮጀክቱ ስደተኞች በስደት ጉዟቸው ውስጥ የጤና ደኅንነታቸውን ለማጠናከር በዲጂታል የሞባይል አፕልኬሽን ባሉበት ኾነው ለማዕከሉ የጤና ባለሙያዎች ችግሮቻቸውን በመግለጽ መፍትሄ የሚሰጥበት መርሐ ግብር መኾኑን አመላክተዋል።

 

ኢኖቬት አሁን ያለውን የ21 ቀን ቅድመ መነሻ ሥልጠና በማጎልበት እና የተዘጋጁ የድጋፍ ዘዴዎችን በማስተዋወቅ የአዕምሮ እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ውጤቶችን ለማሻሻል የተነደፈ የጣልቃ ገብነት ሞዴል መኾኑንም ዶክተር ካሳሁን ሃብታሙ ተናግረዋል።

 

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኢኖቬት ፕሮጀክት ዋና ኀላፊ ዶክተር ሳምራዊት ሰለሞን በበኩላቸው የኢኖቬት ፕሮጀክት ዜጎች በስደት ሕይወታቸው ለሚገጥማቸው ማንኛውም የጤና እክል መፍትሄ ይዞ የመጣ ፕሮጀክት መኾኑን አመላክተዋል።

 

በተለይም ፕሮጀክቱ በሙያ የማብቃት ሥራን ቀድሞ በመሥራት ሠራተኞችን ማሰማራት፤ የአቻ ድጋፍ ሰጭ የራስ አገዝ ቡድኖችን ማቋቋም፤ የጤና መረጃን ለማድረስ ዲጂታል መሳሪያዎችን እና የሞባይል መተግበሪያን የማቅረብ ሥራዎችን ቀድሞ መሥራት እና ስደተኞችም ተመልሰው ሲመጡ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍን በማጠናከር የተጠናከረ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን እንደሚያጎላ ተናግረዋል።

 

ፕሮጀክቱ ስደተኞች በተለይም ሴቶች ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊት፣ በሚሄዱበት ጊዜ እና እንደገና በሚመለሱበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ክፍተቶች እንደሚሞላም ዶክተር ሳምራዊት ሰለሞን ተናግረዋል።

 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ድኤታ ዳንኤል ተሬሳ እንደሀገር ያለው የስደት መጠን መጨመሩን ገልጸዋል።

 

የኢኖቬት ፕሮጀክት እና ክፍሎቹ የስደተኛ ሠራተኞች ጤና እና ደኅንነት ትብብርን ማጠናከር ላይ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

 

በኢትዮጵያውያን ስደተኛ የቤት ሠራተኞች ላይ የጤና፣ የጥበቃ እና የሥነ ልቦናዊ አደጋዎች መስፋፋትን በመቀነስ እና የአዕምሮ ጤና ግንዛቤን በማሳደግ የዲጂታል ግንኙነትን የማጠናከር ሥራውን በትብብር በማስፋፋት ለውጤታማነቱ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

 

በመድረኩ የሠራተኛ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዓለም አቀፍ እና የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ተቋማት፣ ከስደት የተመለሱ የቤት ሠራተኞች፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት እና የሚዲያ አጋሮች ተሳትፈዋል።

 

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያን የከተሜነት ታሪክ የሚመጥን የከተማ ዕድገት እንዲኖር መሥራት ይጠይቃል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ46 ወደ 59 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል።