የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ የት ደረሰ?

7

ባሕር ዳር: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‌የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሀገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለመገንባት የታሰበ ፋብሪካ ነው።

‎‌አቶ ቀናው ገንዘቡ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ‌የፋብሪካው ባለቤቶች እልልታ ኮንስትራክሽን 95 በመቶ ድርሻ ያለው ሲኾን ቀሪው የሁለት ግለሰቦች ድርሻ እንደኾነ ገልጸው ፋብሪካውን ለመገንባት በ2012 ዓ.ም ፈቃድ ወስደው ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

‎‌ፕሮጀክቱ ሁለት ምዕራፍ ያለው ሲኾን የመጀመሪያው በራስ አቅም የሚሠራ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከማሽን አቅራቢዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ከቻይና የሚመጡ ኮንትራክተሮች የሚሠራ ነው ብለዋል።

‎መንገድ፣ ውኃ፣ መብራት ማሟላት፣ ካምፕ ግንባታ፣ የግብዓት መገኛ ቦታዎችን ፈቃድ ማግኘት፣ የአዋጭነት እና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናቶችን መሥራት ‌በራስ አቅም የሚሠሩ ናቸው ብለዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል ሲሚንቶ ለማምረት ግብዓት ለመጠቀም ጥናት ተደርጎ የማዕድን ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

‎‌ወደ ፋብሪካው እና ማዕድን ወደ ሚገኝበት ቦታ የሚወስድ 32 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተሠርቷል፤ ፋብሪካውን ለማሠራት የሚኾን የውኃ፣ የጄኔሬተር መብራት በማሟላት የመኖሪያ ካምፕም ተሠርቶ መጠናቀቁን አንስተዋል።

‎የፋብሪካ አቅራቢዎች ጨረታ ወጥቶ አቅራቢ በመለየት በአጋርነት ከሚሠራ የቻይና ካምፓኒ ጋር ተፈራርመው 51 በመቶ ድርሻ ኖሮት ማሽኑን አምጥቶ በመትከል ሊሠራ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።

‎ይሁንና በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በቻይና ኤምባሲው በኩል ቦታው የግጭት አካባቢ በመባሉ ከዚህ ስጋት ካልወጣ ገብቶ መሥራት እንደሚከለከሉ ገልጸዋል።

‎‌የፋብሪካው ባለሀብቶች የጸጥታው ችግር ፕሮጀክቱን የማይጎዳ እና ለዚህም ዋስትና እንደሚሰጡ ገልጸው አሁንም እንዲገቡ እየተነጋገሩ መኾኑን አንስተዋል።

‎ፋብሪካው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ ችግር እንደሚፈታ እና በቀን 18 ሺህ ቶን ሲሚንቶ በማምረት ለ4 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

‎በመንግሥት በኩል መብራት፣ ውኃ፣ መንገድ እና ቦታውን ካሳ ከፍሎ መሬቱን ነጻ ማድረግ ነበረበት፤ ነገር ግን እነዚህ ተግባራት በባለሀብቶቹ መሠራቱን ተናግረዋል። አሁንም መንግሥት ይከፍላል በሚል የመሬት ካሳ አለመከፈሉን አስታውሰዋል።

‎እስካሁን ቦታው ላይ ካምፕ ተሠርቷል፤ የድንጋይ ወፍጮን ጨምሮ ማሽኖች መኖራቸውን ገልጸው ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠመ ገልጸዋል።

‎አሁን ላይ የተፈረመውን ስምምነት በማክበር እየተጠበቀ ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ በቀጣይ አራት ወራት የማይፈጸም ከኾነ ሌሎች አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

‎‌በቀጣይ ከመንግሥት የሚጠበቁ የፋብሪካ መትከያ ቦታ የካሳ ክፍያ እና ፋብሪካውን የሚያንቀሳቅስ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ነው ብለዋል።

‎‌የምሥራቅ ጎጃም ዞን ማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ መልሰው የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ2012 ዓ.ም የማዕድን ፈቃድ ወስደው ሂደት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

‎‌የሲሚንቶ ፋብሪካው በበረንታ እና በዙሪያው የኾነበት ምክንያት ለሲሚንቶ ግብዓት የሚኾኑ ጅብሰም፣ ኖራ፣ ጥቁር ድንጋይ እና ሌሎች ማዕድናት የሚገኙበት በመኾኑ ነው ብለዋል። የፋብሪካው ባለቤቶች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው የማዕድን ፈቃድ ወስደዋል ነው ያሉት።

‎ከግብዓት ጋር በተያያዘ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የማዕድን ሴክተሩ የሚያደርገው ድጋፍ ነው ያሉት ኀላፊዋ ለፋብሪካው የሚኾኑ መሠረተ ልማቶችን በባለሃብቶቹ መሠራቱንም ገልጸዋል። አሁን ላይ በዞኑ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመው ወደ ሥራ መግባት እንደሚችሉ ለአሚኮ ገልጸዋል።

‎በአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዝናው አበበ የበረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ 170 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲኾን በወቅቱ ከ335 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንደሚያስፈልገው ታውቆ በክልሉ መንግሥት እገዛ ወደ ሥራ እንዲገቡ መታሰቡን ገልጸዋል፡፡

‎ይሁንና በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ አለመገባቱን እና ፋብሪካው የሚገነባበት ቦታ ካሳ ተከፍሎ ነጻ ለማድረግም እንዳልተቻለ ነው የገለጹት፡፡

‎ለሲሚንቶ ግብዓት የሚኾኑ ማዕድናት ማለትም ለኖራ፣ ጀሶ፣ ሸክላ አፈር እና ጥቁር ድንጋይ 285 ሄክታር ላይ ተመርምሮ እና ተጠንቶ ፈቃድ ወስደዋል ነው ያሉት፡፡ ባለሃብቶቹ ግብዓት ወዳለበት ቦታ መንገድ እና የመኖሪያ ካምፕ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡

‎ፋብሪካውን የሚተክለው የቻይና ኩባንያ የጸጥታ ችግሩ ስላሰጋው ወደ ሥራ እንዳልገባ ነው የገለጹት፡፡ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የአካባቢው ሰላም እየተሻሻለ በመኾኑ ወደ ሥራ መግባት ይቻላል ብለዋል፡፡

‎እንደ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ፕሮጀክት ዶክመንቶችን ገምግሞ የማዕድን ቦታዎች ላይ ፈቃድ መሰጠቱን የገለጹት ኀላፊው የአካባቢው የጸጥታ ጉዳይ እየተሻሻለ በመኾኑ ሌሎች አማራጮችንም ተጠቅመው ወደ ሥራ እንዲገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‎በክልሉ የሚደረጉ የማዕድን እንቅስቃሴዎች የጸጥታውን ችግር ምክንያት በማድረግ ወደ ኋላ ሳይሉ ተቀራርቦ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የከተሞቻችንን የዕደገት ጉዞና ተስፋ በግልፅ ያሳየ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleአሶሳ ከተማ 11ኛው የከተሞች ፎረም አዘጋጅ ከተማ ኾና ተመረጠች።