“የሁመራ አየር ማረፊያ አገልግሎት መጀመር ፋይዳው ብዙ ነው” አቶ አሸተ ደምለው

2
ሁመራ፡ ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለበርካታ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የሁመራ አየር መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
አካባቢው የሰላም እና የልማት ቀጣና መኾኑን የተናገሩት የወልቃይት ጠገደ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው። የአየር መንገዱ አገልግሎት መቋረጥ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ኾኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
“የአየር መንገዱ አገልግሎት መስጠት ከዞኑ አልፎ ለአጎራባች ዞኖች ማኅበረሰብም ፋይዳው ብዙ ነው” ብለዋል።
በአካባቢው ያለውን ሰላም በመጠቀም ባለ ሃብቶች ወደ አካባቢው መጥተው በልማት መሳተፍ እንዲችሉ እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በዚህም የዞኑን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃው ነው የገለጹት።
ኅብረተሰቡ ነጻነቱን ካገኘበት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ያህል ያለ አየር መንገድ አገልግሎት ቢቆይም ዛሬ ላይ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ችግሮች በጊዜ ሂደት እየተፈቱ የሚሄዱ ለመኾናቸው ማሳያ ነው ብለዋል።
ዞኑ ሰፊ የንግድ እና የእርሻ ተግባራት የሚከናወኑበት በመኾኑ የአየር መንገዱ በረራ በመጀመሩ አካባቢውን ለማልማት ያስችላል ያሉት ደግሞ አየር መንገዱ ላይ ያገኘናቸው ተሳፊሪ ወንድም ገብረ መድኅን ናቸው። በጸጥታ ችግር የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች አስቸጋሪ በኾኑበት ጊዜ ላይ አየር መንገዱ ትልቅ አማራጭ ነውም ብለዋል።
የአገልግሎቱን መጀመር በጉጉት ሲጠብቁ መቆየታቸውን ሌላኛዋ ተሳፋሪ አዳነች አሳምረው ናቸው። አካባቢው ከአዲስ አበባ እርቆ የሚገኝ በመኾኑ የሁመራ አየር መንገድ ሥራ መጀመር የኅብረተሰቡን የትራንስፖርት ችግር እንደሚቀርፍም አንስተዋል።
አየር መንገዱ በረራ የጀመረው በሳምንት ለሁለት ቀናት ሲኾን ከአዲስ አበባ ሁመራ የበረራ መነሻ እና መዳረሻ መኾኑም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየከተሞች ፎረም የማጠቃለያ መርሐ ግብር በሰመራ ሎጊያ ከተማ እየተካሄደ ነው።