
ደሴ: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ ከ77 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) እና በጀርመን መንግሥት የተሠራ ነው።
በላሊበላ ከተማ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር የረጅም ጊዜ የማኀበረሰቡ ጥያቄ እንደነበር ያነሱት የከተማው ነዋሪዎች ውኃ ለማግኘት እስከ አስር ቀን ይጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት ሥራ ከጀመረ በኋላ ግን በየዕለቱ ውኃ ማግኘት መጀመራቸውን ነዋሪዎቹ አንስተዋል። ይህንን በጎ ተግባር የከወነውን እና ለዘወትር ጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠውን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበርንም አመስግነዋል።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዩጵያ ልዑክ መሪ ሲሞን ካዛቢያንካ የተመረቀው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና በጀርመን መንግሥት ድጋፍ ከ2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በኾነ ወጭ መገንባቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል በአፍሪካ ከተሠሩ የሶላር ፕሮጀክቶች ትልቁ ፕሮጀክት መኾኑንም አስረድተዋል። የላሊበላ ማኅበረሰብ የረዥም ጊዜ ጥያቄ የኾነው የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር መልስ በማግኘቱ እጅግ መደሰታቸውንም ተናግረዋል።
የላሊበላ ከተማ ንጹሕ መጠጥ ውኃ መልሶ ግንባታ እና ሶላራይዜሽን ፕሮጀክት ስድስት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች፣ 3 የውኃ መሳቢያ ፓምፖች፣ 12 የውኃ ማሰራጫ ፓምፖች ያሉት ነው።
4 መጠባበቂያ ጀነሬተሮች፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የውኃ ማጣሪያ ሥርዓት እና የውኃ ጥራት መቆጣጠሪያ ቤተ ሙከራን ያቀፈ እንደኾነ የገለጹት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ የላሊበላ ከተማ የውኃ ፕሮጀክት ኀላፊ ኢንጂነር ዘሪሁን ለገሰ ናቸው።
በቀን እስከ 2 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ መስጠት እንደሚችል የተናገሩት ኢንጂነር ዘሪሁን ፕሮጀክቱ ከ77 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። የሶላር ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ወጭን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀርም አስረድተዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የውኃ መሠረተ ልማቶች መውደም፣ ከኤሌትሪክ ኃይል እጥረት ጋር ተያይዞ በቂ የኾነ ውኃ ለማኀበረሰቡ ለማድረስ ፈታኝ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የላሊበላ ከተማ ውኃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መለሰ አየለ የተመረቀው የሶላር ውኃ ፕሮጀክት ችግሩን መቅረፍ ማስቻሉን አስረድተዋል።
የላሊበላ ከተማ ከንቲባ መሳይ ወዳጄ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና የጀርመን መንግሥት የማኀበረሰቡን ችግር በመረዳት ለሠሩት ተግባር አመስግነዋል። የሶላር ፕሮጀክቱ የላሊበላን ሕዝብ የረዥም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ መመለስ የቻለ ነውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አረጋ ካሳ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር የክልሉን መንግሥት ፕሮጀክቶች በማገዝ በኩል ቀዳሚ መኾኑን ተናግረዋል። በሰሜኑ ጦርነት በዘርፉ የደረሰው ውድመት መጠነ ሰፊ በመኾኑ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እገዛ አሁንም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
