
አዲስ አበባ: ኅዳር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ10ኛው የከተሞች ፎረም ድርጅቶች እና ግለሰቦች የፈጠራ ሥራቸውን እያስተዋወቁ ናቸው።
አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ይዘው ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል የገቡ አንድ ድርጅት እና አንድ ግለሰብ በፈጠራ ሥራዎቻቸው ዙሪያ አሚኮ አነጋግሯል።
ወጣት ሙክታር ሁሴን በአማራ ብረታ ብረት ኮምቦልቻ የግብርና ግንባታ ማምረቻ ማዕከል የማርኬቲንግ ባለሙያ ሲኾን በድርጅቱ የተመረተ የፈጠራ ሥራን በሰመራ ሎጊያ በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ሲያሰተዋውቅ ነው አሚኮ ያገኘው።
በቆሎ አምራች አርሶ አደሮች የደረሰ በቆሎን ለመሠብሠብ ብዙ ድካም ይገጥማቸዋል። በአማራ ብረታ ብረት ተመርቶ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ማሽን በቆሎ ሳይላጥ ወደ ማሽኑ በመጨመር ፍሬውን ከገለባው የሚለይ ማሽን ነው።
ማሽኑ በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ ይሠራል። ትራክተር ያላቸው ሰዎች ከትራክተር ጋር ተገጥሞ በቆሎውን መፈልፈል ያስችላል።
በቦታው አሚኮ ባደረገው ምልከታ ያልተላጠ በቆሎን ወደ ማሽኑ በማስገባት በፍጥነት እና በጥራት ሲፈለፍል መመልከት ችሏለል።
ይህ ማሽን አርሶ አደሮች በቆሎ በሚያመርቱበት ጊዜ በቆሎን ለመላጥ እና ለመውቃት ቀናትን የወሰደ አድካሚ ሥራን የሚያቃልል ነው።
የማርኬቲንግ ባለሙያው ሙክታር ሁሴን ማሽኑ ለገበያ ቀርቦ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሷል።
በሌላ በኩል አቶ ውብሸት ታየ በጎንደር ከተማ በእንጨት እና በብረታ ብረት ማምረት የተሰማሩ ግለሰብ ናቸው። አቶ ውብሸት ያመረቱትን ማሽን በከተሞች ፎረም ሲያስተዋውቁ ነው አሚኮ ያገኛቸው።
አቶ ውብሸት ባለብዙ አገልግሎት ማሽን በራሳቸው ሠርተዋል። የሥራቸውን ውጤትም በ10ኛው የከተሞች ፎረም ከጎንደር ከተማ ልዑካን ጋር በመኾን በሰመራ ሎጊያ ከተማ ምርቱን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
አቶ ውብሸት ያቀረቡት ማሽን በቆሎ መፈልፈያ፣ የተፈለፈለውን የሚፈጭ እና የሚከካ ብሎም የበቆሎን አገዳ እና ሌሎች ውጤቶችን በመፍጨት ለእንስሳት መኖ እንዲውል የሚያግዝ ማሽን ነው።
ይህ ማሽን እንስሳትን ለሚያደልቡ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች እንስሳትን የሚያረቡ አርሶ አደሮች ቢኖሩም መኖን ቆጥቦ ለመጠቀም ለእንስሳት ቆራርጦ እና ፈጭቶ መስጠት የመኖ ብክነትን ያስቀራል።
የተሠራው ማሽን በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ እንዲሠራ ኾኖ የተዘጋጀ ነው። ያዘጋጁትን ፈጠራም ከአጋር አካላት ጋር በመኾን በብዛት ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
