
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውን የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አስመልክተው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመግለጫቸው እንዳመላከቱት ግብጽ ከዚህ በፊት በድርድሩ ስታሳየው የነበረውን ሙሉ የዓባይ ውኃ ይገባኛል አካሄድ አሁንም እየተከተለች ነው፡፡ በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የተከተሉት ይህ አካሄድ ለአሁኑ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በምንም መልኩ የማያስኬድና የማንቀበለው ነው ብለዋል አቶ ገዱ በመግለጫቸው፡፡
ግብጽ አሁንም ፍላጎቷ ድርድሩ እንዲቋረጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በ2015 (እ.አ.አ) ከነበረው የመርህ ስምምነት ውጭ ሌላ መተሳሰሪያ የሌለን በመሆኑ ግብጽ ድርድሩን አቋርጣ የምትወጣ ከሆነ ከዚህ በኋላ ለድርድር የምንቀመጥበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
እየተደራደርን ያለነው ሁሌም እኔ ብቻ ልጠቀም ከምትለው፣ እድሜ ልኳን የኢትዮጵያን ጥቅም ከምትጻረረው፣ ሀገራችን ዘላቂ ጥንካሬ እንዳይኖራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከምትሠራው ግብጽ ጋር ነው ሲሉም አቶ ገዱ የግብጽን አቋም አስረድተዋል፡፡
የግብጽ ሕዝብ መንግሥታቸው ምክንያታዊና ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ተመስርቶ እንዲደራደር ጫና እንዲያሳድሩም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
