
ባሕርዳር፡ ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ በመኾን አዲስ የገቢ ግብር አዋጅ ረቂቅ ላይ ውይይት አድርጓል።
ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ነው የገቢ ግብር አዋጅ፣ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ፣ የኤክሳይዝ ታክስ፣ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ሥራ የገቢ ግብርን የተመለከቱ ረቂቅ አዋጆች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው።
ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማድረግ፣ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ አሠራር የሚያስቀር ቀላል፣ ምቹ እና ችግሮችን እንዲፈታ ተደርጎ መዘጋጀቱ፣ በፊት ላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ሲባል የነበረው አሠራር በማስወገድ በሚመች መንገድ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ መዘጋጀቱ በተሳታፊዎች በኩል የተነሱ አዋጁን የሚደግፉ ሀሳቦች ናቸው።
የግብር ሥርዓቶችን ለግብር ከፋዮች ምቹ እንዲኾኑ ማድረግ፣ መተማመንን የሚያመጣ የግብር አከፋፈል ሥርዓት መከተል፣ የማኅበረሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የገቢ ግብር አዋጅ እንዲኖር ማድረግ፣ የኤክሳይዝ ታክስ፣ ዓመታዊ ሽያጭና የግብር የመክፈል አቅምን ማጣጣም፣ የፍትሐዊነት ጉዳዮች፣ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ሥራ የገቢ ግብርን የተመለከቱ ረቂቅ አዋጆች ትኩረት እንዲደረግባቸው በተሳታፊዎች የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሃናን አብዱ ረቂቅ አዋጁ ለአማራ ክልል ምክር ቤት እስከሚቀርቡበት ጊዜ ድረስ አስተያየት እየተሰጠበት እና እየተሻሻለ እንደሚሄድ ተናግረዋል። በተለያዩ አማራጮች ሕዝቡ አስተያየት እንዲሰጥበትም ለገቢ ተቋሙ አቅጣጫ ሰጠዋል። ያለገቢ ግብር እድገት አይኖርም ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በቀጣይም የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ ተመሳሳይ ውይይት ምስራቅ አማራ ላይ በደሴ ከተማ እንደሚኖር ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የአማራ ክልል የገቢ ማሰባሰብ አቅምን ሊያሳድግ የሚችል ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። በርካታ ክፍተቶችን የሚሞላ ተደርጎ ተዘጋጅቷልም ነው ያሉት።
ይህ አዋጅ ብዙ ዓመት ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየ ነበር ያሉት ኀላፊው በአዋጁ ስር ያሉ አንዳንዶቹ አዋጆች ከ20 ዓመት በላይ የቆዩ መኾናቸውን አስታውሰዋል። በቆየው እሳቤ የተዘጋጁ ከመኾናቸው ጋር ተያይዞ አሁን ላይ መከለስ አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት። በታክስ መርሆች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን ዋና አላማቸው እንደኾነም አንስተዋል።
በአዲሱ አዋጅም ዘመኑ ያፈራቸው የዲጂታል ይዘት ያላቸው ሀሳቦች የተካተቱበት መኾኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት በወጣው አዋጅ ላይ ያልታወቁ ገቢዎችን የተመለከተው ጉዳይ ቀጣይ ራሱን ችሎ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱንም አንስተዋል። ወደፊትን አርቆ ማየት እንዲቻል ተደርጎ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። በርካታ የሀብት አማራጮችን የሚያይ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ከገቢ ግብር አዋጅ ጋር ተያይዞ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ተቆጥረው መፈታት እንዳለባቸው ተናግረዋል። መንግሥት የማያውቃቸው ክፍያዎች መታረም እንዳለባቸውም አንስተዋል። ሕጋዊነት ከሌለ ግብር መሠብሠብ እንደሚያስቸግርም ጠቅሰዋል። ትክክለኛ ግብር ካልተሰበሰበ የሥራ እድል መፍጠር፣ ልማት ማልማት እና ምርታማነትን ማሳደግ አይቻልምም ነው ያሉት። በቀጣይ ትክክለኛ ግብር ከፋዮች እየተደገፉ እና እየተበረታቱ እንደሚሄዱ ነው የተናገሩት።
በውይይቱ የተገኙ ሀሳቦችም ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር በግብዓትነት ይውላሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
