
ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ከተማ አቀፍ የባሕላዊ ሽምግልና መማክርት መመስረቻ ጉባኤን በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ዛሬ የሚመሠረተው የባሕላዊ ሽምግልና መማክርት ጉባኤ የሚፈጠሩ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እና ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላም በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
የቀድሞ አባቶች በባሕላዊ ሽምግልና ትልልቅ የተባሉ ችግሮችን በቀላሉ ይፈቱ እንደነበርም አስረድተወዋል።
ዛሬ ላይ ይህ የሽምግልና ሥርዓት ተቀዛቅዞ በሚፈለገው ልክ እየተተገበረ አይደለም። ይህንን የባሕላዊ ሽምግልና አጠናክሮ ለመቀጠል የመማክርት ጉባኤው ተቋቋሟል።
በቀጣይ በከተማው ባሉ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመረጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የባሕላዊ ሽምግልና መማክርት ይቋቋማል ነው ያሉት።
በመክፈቻው የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
