በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።

3

ደባርቅ: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለመጠበቅ እና በውስጡ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳትን ለመንከባከብ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናዎነ እንደሚገኝ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

የጽሕፈት ቤቱ ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ ለማኅበረሰቡ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በፓርኩ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በዘላቂነት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋርም በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡ የባለቤትነት ድርሻ ወስዶ በእኔነት ስሜት የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን እንዲያከናውን ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎች መሰጠቱን ተናግረዋል። የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መገባቱንም አክለዋል።

ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ለማሳደግም እየተሠራ ነው ብለዋል።

የፓርኩ ሕግ የማስከበር ቡድን መሪ ሲሳይ ሰለሞን በፓርኩ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት የመፍትሔ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

የፓርኩን የጥበቃ ቡድን አባላት በተለያዩ ንድፈ ሀሳባዊ እና ተግባራዊ ሥልጠናዎች የማብቃት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱን የማሻሻል እና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አክለዋል።

በፓርኩ የቅኝት አገልግሎትን በተጠናከረ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የፓርኩ የሥነ ምኅዳር ክትትል እና ማበልጸግ የሥራ ሂደት ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ የፓርኩን ደኅንነት እና የዋልያ ቁጥርን ለማሳደግ የሚያስችል የዋልያ መልሶ ማገገም ዕቅድ (ዋልያ ሪከቨሪ ፕላን) ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።

በዋልያ ቁጥጥር እና እንክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ቡድኖችን በማቋቋም ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም የፓርኩን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሁለንተናዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአካባቢያችን ያሉ አቅመ ደካሞችን ልንደግፍ ይገባል፡፡
Next articleየባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።