በአካባቢያችን ያሉ አቅመ ደካሞችን ልንደግፍ ይገባል፡፡

2

ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ታገኝ ምኅረቱ በባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ሽምብጥ ቀበሌ ከ30 ዓመት በላይ ነዋሪ ናቸው፡፡

ወይዘሮ ታገኝ እንጀራ በመጋገር፣ ልብስ በማጠብ እና ሌሎችንም ሥራዎች እየሠሩ ኑሮን እንደነገሩ ይገፉ እንደነበር ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይኖሩበት የነበረው ቤት ጣራው ተቀዶ እና ግድግዳው ፈርሶ ዝናብ የሚያስገባ ስለነበር ቤቱ በሚፈጥረው ቅዝቃዜ ለሕመም መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው ቤት እንደሚውሉ ነው የነገሩን፡፡

ወይዘሮዋ ቤቱ በመፍረሱ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ቀና ልብ ባላቸው ሰዎች ግድግዳውን የመምረግ እና የማስተካከል ሥራ ቢሠራም በጣም አርጅቶ ስለነበር የነበረው ችግር አልተቀረፈም፡፡

አሁን ግን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሠራተኞች ቤታቸውን ሙሉ በሙሉ አድሰውላቸዋል። ቤቴ ተሠርቶ አምሮበት፣ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችም ተሟልተውልኝ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል ነው ያሉት ወይዘሮ ታገኝ፡፡

ይህንን ድጋፍ ላደረጉልኝም ትልቅ አክብሮት አለኝ፤ በጣም አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ አጠቃላይ የቢሮው ሠራተኞች ከኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት የወይዘሮ ታገኝን ቤት ሠርተን በማስረከባችን እኛም ደስ ብሎናል፤ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ሥራውን ስናስጀምር ሁሉንም ሠራተኞች በማወያየት ይሁንታቸውን በማግኘት ነው ወደ ሥራ የገባነው ብለዋል፡፡

ለቤቱ ግንባታ፣ ለቤት ቁሳቁስ፣ ለአልባሳት እና ለጊዜያዊ ምግብነት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ጨምሮ ከ721 ሺህ ብር በላይ ወጭ ተደርጎበታል ነው ያሉት አቶ አብዱልከሪም፡፡

በቀጣይም እንደዚህ አቅማቸው የደከሙትን እና ድጋፍ የሚሹትን ሰዎች በመለየት ሠራተኞችን በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህ ትብብር ቀና ኾነው ድጋፍ ያደረጉ ሠራተኞችንም በቢሮው ስም ምሥጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን በክልሉ በክረምት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

በተለይም በከተማዋ የሚገኙ ለመኖር አስቸጋሪ የኾኑ የፈራረሱ ቤቶችን የመጠገን እና ሙሉ በሙሉ የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሠራተኞችም ገንብተው ዛሬ ያስረከቡት ቤት ለመኖር አስቸጋሪ ከነበሩ ቤቶች መካከል አንዱ ሲኾን ሠራተኞቹ ይህንን ተግባር በቀናነት ማከናወናቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል።

በቀጣይ ሌሎች ተቋማት እና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ይህንን በጎ ተግባር እንደ አርዓያ በመውስድ ድጋፍ ከሚሹ ወገኖቻችን ጎን መቆም ይኖርብናልም ብለዋል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ይህንን ሀሳብ ያመነጩት፣ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን እና ያስተባበሩትን አካላት አመስግነዋል፡፡

ታላላቆችን ከማክበር እና ከመታዘዝ ባለፈ አቅማቸው ሲደክም መውደቂያቸውን ማየት እና መደገፍ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ሰው ተኮር ተግባራት ማሳያዎች ነው ብለዋል፡፡

ዛሬም ይህንን ቤት የጤና ቢሮ ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች አሥተባብረው ሲሠሩት እኛን አስተምረው አሁን ላይ የእኛን ድጋፍ የሚሹ አዛውንቶች፣ እናቶች፣ ችግረኛ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሰብ እንዲኾን ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ በመኾን የቤት ችግር ያለባቸውን አቅመ ደካሞች ለመደገፍ ያስችላል የሚል መልዕክት ያስተላልፈ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ የወይዘሮ ታገኝን የቤት ችግር ፈተናል፡፡በቀጣይም ሁሉም ቢሮዎች እንደየአቅማቸው በሃሳብ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ ሰው ተኮር የኾኑ ሥራዎችን እያዳበርን ልንሄድ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሮችን ከባሕር ዛፍ ልማት ወደ ሙዝ ምርት እንዲሸጋገሩ በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
Next articleበስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።