
አዲስ አበባ፡ ኅዳር 09/2018ዓ.ም (አሚኮ)
14ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ኮንፍረንስ “የእሴት ሰንሰለቶቻችንን እያዳበርን ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቻችንን ማስፋት” በሚል መሪ መልዕክት መካሄድ ጀምሯል።
ከ500 በላይ የሀገር ውስጥ ላኪዎች፣ ከ17 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ገዥዎች በኮንፈረንሱ ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው የ2017 በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አግኝታለች። ከዚህ ውስጥ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ይጠጋል።
ይህን ድርሻ ማሳደግ እና ሀገሪቱ ያላትን ምቹ ሁኔታ ማስተዋወቅ ብሎም የንግድ ተስስር መፍጠርን ኮንፈረንሱ ዓላማ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና የቅመማ ቅመም ላኪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤዳኦ አብዲ ኮንፍረንሱ ምርትን ከማስተዋወቅ ባሻገር የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እና የገበያ መዳረሻ ሀገራትን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳዮችን በማሻሻል፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ፣ የካፒታል ገበያን በመክፈት፣ ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሃብቶች ነጻ የማድረግ እና ሌሎች ርምጃዎችን መውሰዱ ዘርፉን እያነቃቃው መኾኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ኮንቲኔንታል ነጻ የንግድ ቀጣና መጀመር የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በኤክስፖርት ንግድ ለውጥ እንዲያመጡ ያስችላል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘርፉ የበርካታ ዜጎች የሕይዎት መሠረት እንደኾነ ጠቁመዋል። የሥራ ዕድልም ተፈጥሮበታል ነው ያሉት።
ይበልጥ ተጠቃሚነትን ለማሳደግም አሠራሮችን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ ማሻሻል እና ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) እንደተናገሩት በጥራጥሬ እና በቅባት እህሎች ዐውድ ውስጥ የእሴት ሰንሰለቶችን ማጠናከር ወሳኝ ነው።
በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚ እንደሚኾኑም አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ የምርት ቴክኒኮችን ለማሻሻል፣ የአቅርቦት ሰንሰለት ሎጅስቲክስን ለማሳደግ እና የተሻለ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፈን ቴክኖሎጂን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
በጋራ የገበያ ውጣ ውረዶችን እና የአየር ንብረት ለውጥን ጫና የሚቋቋም ጠንካራ እና ተስማሚ የእሴት ሰንሰለት መገንባት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ዓለም አቀፋዊ መሪ ለመኾን ያላትን የማያወላውል ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማነቃቃት ቁልፍ ማሻሻያዎችን እያካሄደች ነውም ብለዋል። ለጥራት እና የጋራ ትብብር ልዩ ትኩረት በመስጠቷ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ማስፋት አስችሏታል ነው ያሉት።
በዘርፉ በትኩረት በመሠራቱ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች የውጭ ንግድ እያደገ መምጣቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ኮንፈረንሱ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ እና የንግድ ትስስሮች፣ የልምድ ልውውጦች እና ውይይቶች እንደሚካሄዱበትም ታውቋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
