
ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሩዝ አብቃይ ከሚባሉ ቦታዎች መካከል ፎገራ ወረዳ እና አካባቢው ተጠቃሽ ነው። በፎገራ ሩዝ በብዛት ይመረታል። ነገር ግን የሩዝ ምርት የጥራት ችግር እንደሚስተዋልበት ይነሳል። ሩዝን በጥራት ተወዳዳሪ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?
በፎገራ ወረዳ ሩዝ አምራች የኾኑ አርሶ አደር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአካባቢያቸው አራት አይነት ሩዝ እንደሚመረት ነግረውናል። ነጭ ሩዝ የሚባለው ደግሞ ገበያ ላይ ተፈላጊ እንደኾነ ገልጸዋል።
የፎገራ ሩዝን በጥራት ለማምረት ዋናው መፈልፈያው ነው ያሉት አርሶ አደሩ ያመረቱትን ሩዝ በባለሃብቶች ማሽን በክፍያ አስፈልፍለው እንደሚሸጡት አንስተዋል።
በሚፈለፈልበት ጊዜ ተረፈ ምርቱ ለእንስሳት መኖ ስለሚፈለግ የሚፈለፍሉ አካላት የሩዙን ክፍል ወደ ተረፈ ምርቱ እንዲሔድ ያደርጉታል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ የሩዙን ጥራት ይቀንሰዋል፤ አርሶ አደሮችም ከተረፈ ምርቱ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ያደርጋል ብለዋል።
የፎገራ ሩዝ በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ይመረታል። በገበያ ላይ ግን ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ጥራቱ እና ዋጋው ዝቅ ያለ ነው ብለዋል። ምክንያቱ ደግሞ የመፈልፈያ ማሽኑ ጥራት አነስተኛ በመኾኑ ነው፤ መንግሥት እና ባለሃብቶች የተሻለ ጥራት ያለው ማሽን እንዲያስገቡም ጠይቀዋል።
በፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ ገብሬ ታምር በወረዳው በሰፊው የሚመረተውን ሩዝ ጥራት ለማስጠበቅ በግብርናው ዘርፍ ከእርሻ እስከ ጉርሻ በሚል ለአርሶ አደሮች ሥልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት።
ለጥራቱ መቀነስ የፎገራ እና አካባቢው ሩዝ የዝርያው ባህሪ በሚፈለፈልበት ጊዜ የመድቀቅ ሁኔታ ያለው መኾኑ እና የዝርያውን ባህሪ መሠረት አድርጎ የሚፈለፍል ማሽን አለመኖር እንደ ምክንያት አንስተዋል።
በሚፈለፈልበት ጊዜ ምርቱ በጥራት ሳይለይ ተደበላልቆ መፈልፈሉ፣ ገበያ ላይ የሩዝ ዋጋ ደረጃ ያልወጣለት በመኾኑ፣ አምራቾች ሲሸጡ ጥራት ያለውም የሌለውም በተመሳሳይ ዋጋ መሸጡ ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው የገለጹት።
ሩዝ የመፈለፈል አገልግሎት የሚሰጡት የግል ባለሃብቶች በመኾናቸው ከተረፈ ምርቱ የሚያገኙትን ጥቅም በማሰብ ለዋናው ምርት ከመጠንቀቅ ይልቅ በማድቀቅ ወደ ተረፈ ምርቱ እንዲሄድ መደረጉ የሩዝ ጥራት እንዳይኖረው ያደርጋል ነው ያሉት።
ይህም የሩዝ ምርቱ በጥራት እና በዋጋ ተወዳዳሪ እንዳይኾን እና አርሶ አደሮችም ባመረቱት ልክ ተጠቃሚ እንዳኾኑ አድርጓል ብለዋል። ከዚህ በፊት በረጅ ድርጅቶች የቀረቡ የመፈልፈያ ማሽኖች በቦታ እና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ለሩዝ የተሻለ ትኩረት በመሰጠቱ ጥራቱ ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።
በተያዘው የምርት ዘመን በወረዳው 44 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ተሸፍኗል፤ ከዚህም ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የፎገራ ሩዝ ምርምር እና ሥልጠና ማዕከል የብሔራዊ ሩዝ ምርምር ፕሮግራም አሥተባባሪ ሙሉጌታ አጥናፍ (ዶ.ር) ማዕከሉ የሩዝ ምርምር ፕሮግራሙን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሥተባብራል ነው ያሉት።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 40 አይነት የሩዝ ዝርያዎች ሰላም፣ ሻጋ እና ጉማራ የሚባሉ ዝርያዎች ለፎገራ እና አካባቢው መልክዓ ምድር ተስማሚ እና በስፋት የሚመረቱ እንደኾኑ አስረድተዋል።
የሩዝ ምርት ጥራትን ለማምጣት ከአመራረት ሂደት ጀምሮ አሰባሰቡ እና እስከሚፈለፈልበት ድረስ ያለው ሂደት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
በገበያ ላይ በጥራት ተወዳዳሪ እንዲኾን ለማድረግ የድህረ ምርት ሂደት ተጽዕኖው የጎላ መኾኑንም አንስተዋል።
የፎገራ እና አካባቢው ሩዝ ብዙ ጊዜ የተሰባበረ ነው፤ ለዚህ ምክንያቶቹ የዝርያው ባህሪ፣ ተገቢውን የማምረት ሂደት አለመከተል እና ከተሰበሰበ በኋላ ደረጃውን በጠበቀ ማሽን አለመፈልፈል ናቸው ነው ያሉት።
አርሶ አደሮች ሩዝ የሚሸጡት ከተፈለፈለ በኋላ ነው፤ ሲፈለፈል ተረፈ ምርቱ ለእንስሳት መኖ ይውላል፤ በሂደቱ ላይ እንዲሰባበር የማድረግ የአሠራር ችግር አለ ብለዋል።
አርሶ አደሮች ያልተፈለፈለውን ሩዝ በመሸጥ ቀጥሎ ያለውን ሂደት ሌላው አካል ሠርቶ ለገበያ ማቅረብ ቢቻል መፍትሔ ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ሩዝ ፍጆታው ከፍተኛ ነው፤ እንደ ሀገር የማምረት አቅም ስላለ የሩዝ ምርትን በጥራት አምርቶ በማቅረብ ከውጭ የሚገባውን ማስቀረት እንደሚቻልም ገልጸዋል። ሩዝ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ሰብል ኾኗል፤ ይህ ደግሞ ጥራቱ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ያግዛል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ እንየ አሰፋ የሩዝ ምርት በየዓመቱ ሽፋኑ እየጨመረ የመጣ ምርት መኾኑን አንስተዋል።
የጥራት ችግር የሚፈጠረው የሰብል አሰባሰብ እና የመፈልፈል ሂደት ላይ መኾኑን ነው የገለጹት። በሩዝ ምርት ላይ የድህረ ምርት ቴክኖሎጅ አቅርቦት ውስንነት በመኖሩ እስካሁን ድረስ በባሕላዊ መንገድ የሚፈለፍሉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ ክልል በረጂ ድርጅቶች አማካኝነት ጥራት ያላቸው ስምንት የመፈልፈያ ማሽኖች ለተለያዩ ወረዳዎች ተሠራጭተዋል ነው ያሉት። ይህ ተግባር እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
የሩዝ ምርትን ጥራት ለማስጠበቅ በተገቢው መንገድ ከማምረት ቀጥሎ አሰባሰቡ እና የመፈልፈል ሂደቱ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደኾነም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች በጋራ ኾነው ማሽን የሚያገኙበትን እና በራሳቸው እንዲጠቀሙ ማስቻል ሌላው መንገድ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
