
ባሕር ዳር: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ በዓል አክብሯል።
በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ “የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተከበረው።
በበዓሉ ላይ የሚመለከታቸው የሥራ መሪዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሕጻናት ተሳትፈዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙ ሕጻናት በመጫወቻ ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። በመድረኩ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ቀርቧል። የተማሪዎች የጥያቄ እና መልስ ውድድርም ተካሂዷል።
የበዓሉ ተሳታፊ ሕጻን ሐብታሙ መልኬ በዓሉን በተለያዩ ጨዋታዎች እና በጥያቄ እና መልስ ውድድር መሳተፉን እና ደስተኛ መኾኑን ነግሮናል።
የአማራ ክልል የሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሕጻን ተምኪን ይሃ ሕጻናት የመጫወት እና ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው ብላለች። ጨዋታ ልጆች ከሰዎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት እና የስሜት ልህቀት የሚያሳድጉበት በመኾኑ የተሟላ ዕድገት እና ደኅንነት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስታለች።
ስለዚህ ልጆች የልጅነት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲያሳልፉ የመጫወቻ ቦታዎች ሰላማዊ እና ከአደጋ የራቁ እንዲኾኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።
ለሕጻናት ጥበቃ እና ጨዋታ ማግኘት መብት እንጅ ቅንጦት አለመኾኑን በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት የሕጻናትን መብት ለማስከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቃለች።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ በዓሉ በየደረጃው በተለያዩ ዝግጅቶች በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች እና በዞኖች ሲከበር ቆይቷል ብለዋል።
በክልሉ በርካታ ሕጻናት በችግር ውስጥ ኾነው የሚማሩ፣ ትምህርት የማያገኙ እና ጥቃት የሚደርስባቸው አሉ ብለዋል። ስለዚህ ይህ በዓል በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች የሚሠሩ ሥራዎችን በማጠናከር ሕጻናት ደኅንነታቸው፣ ጤንነታቸው እና አካላዊ ብቃታቸው የተጠበቀ ኾነው እንዲያድጉ ብዙ ሥራዎች እየተሠራበት መኾኑን ተናግረዋል።
ሕጻናት የዴሞክራሲ ሥርዓት መብታቸውን እንዲለማመዱ በሕጻናት ፓርላማ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለሕጻናት ጤናማ እና ለኑሮ ምቹ፣ ተስማሚ አካባቢ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መሠራት ስላለበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ለሕጻናት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሕጻናት የአንድ ሀገር የወደፊት ተስፋ እና ሀብት ናቸው ብለዋል። ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ላይ መሥራት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በማኅበራዊ ኑሮ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ወጥ የኾነ አደረጃጀት ተዘርግቷል፤ በሕጻናት ዙሪያ የተጠናከረ የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን በየዓመቱ ኅዳር 11 ቀን ይከበራል ያሉት ኀላፊዋ ቀኑን ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት መንግሥታት ተገቢውን አጽንኦት በመስጠት በሚያወጧቸው ፖሊሲዎች የሕጻናትን ጉዳይ እንዲያካትቱ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በዓሉ በክልሉ ሲከበር ስለሕጻናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። የሕጻናት ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲሁም የመጫወቻ ቦታዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በየአካባቢው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተሠርቷል ነው ያሉት።
የሕጻናት ቀን ሁነቶች ሕጻናት ተሰባስበው በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት በመኾኑ በክልሉ ለሁለት ወራት በተለያዩ ሁነቶች እስከ ወረዳ ድረስ ሲከበር ቆይቷል ብለዋል፡፡
በሀገራችን በርካታ ሕጻናት ለደኅንነታቸው ተቃራኒ ለኾኑ አደጋዎች ተጋልጠው ይገኛሉ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።
የሀገር ተረካቢ ሕጻናት ከችግር ተላቀው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ እና ሀገር ወዳድ ዜጎች እንዲኾኑ የሚመለከታቸው አካላት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ የተማሪዎች ጥያቄ እና መልስ ውድድር ተካሄዶ ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ለበዓሉ ትብብር ላደረጉ አካላትም ዕውቅና ተሰጥቷል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
