
አዲስ አበባ: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ አከባበር እና የራስገዝነት ሪፎርምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ኾኖ ከተመሠረተ 75 ዓመታትን አስቆጥሯል።
የዩኒቨርሲቲው ምሥረታ የአልማዝ ኢዮቤልዮ በዓል ዩኒቨርሲቲው ለረዥም ጊዜ ሲጠይቅ ከነበረው ራስገዝነት መፈቀድ ጋር በጥምረት እንደሚከበርም ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 75 ዓመታት ያካበተውን አቅም ለአካዳሚክ፣ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአገልግሎት ልማት ለማዋል ራስገዝነት የሚሰጠውን አቅም ለመጠቀም በመዘጋጀት በርካታ ሥራ እየሠራ እንዳለ ገልጸዋል።
ታኅሣሥ 1943 ዓ.ም 50 ተማሪዎችን ይዞ በአብዛኛው በውጭ ሀገር መምህራን ሥራ የጀመረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ በሀገር እና በአሕጉር ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ማፍራት የቻለ ዩኒቨርሲቲ እንደኾነም ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ካሉ ጠንካራ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ለመኾን የያዘውን ውጥን ወደ ማሳካት እንደተቃረበም አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባለፉት ዓመታት ያካበተውን ወረት እና አቅም እሠባሥቦ መጭውን ዘመን በሚመጥን መልኩ ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በዚህም መነሻ የዚሁ የ75ኛው ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል መሪ መልዕክት “ያለፈውን በማክበር የተሻለ ነገን መፍጠር” በሚል መመረጡን ገልጸዋል።
ባሳለፋቸው 75 ዓመታት ባካበተው አቅም እና ወረት ከ170 በላይ ሙሉ ፕሮፈሰሮች ያሉት፣ ከ10 ሺህ በላይ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የሚያስተናግድ፣ በዓመት ወደ 1ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የፈውስ እና እንክብካቤ መስጠት የሚችል ሆስፒታል ያሉት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት እና ምርምር ተቋምነት ባለፈ እንደ አንድ የሀገር ወካይ ተቋምም ኀላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኅዳር እና በመጭው ታኅሣሥ ወር ሌሎች ለአልማዝ ኢዮቤልዮ ማክበርያ የታቀዱ ኩነቶች እና ዝግጅቶች እንዳሉትም ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የራስ ገዝ ሪፎርም ማስጀመሪያ እንዲኾን ተወስኖ በአዋጅ 1294/2015 እና ተከትሎ በወጣው ደንብ 537/2016 መሠረት በመተግበር እንደ ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ (መልሶ) ተቋቁማል ነው ያሉት፡፡
በአዋጁ ወደ ራስገዝነት የሚደረገው ሽግግር ጊዜ የሚጠይቅ እና የሁለት ዓመት የሽግግር ጊዜ ተሰጥቶ እንዲፈጸምም ተደንግጓል፡፡
በዚሁ መሠረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስገዝነት ለመሸጋገር የሚረዱትን ተግባራት በባለፉት 24 ወራት ሲፈጽም እንደቆየ ገልጸዋል።
የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ልማት መመሪያ፣ የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር መመሪያ፣ የፋይናንስ አሥተዳደር መመሪያ፤ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መመሪያ፣ የመሪ እና ፈፃሚዎች ምደባ፣ የደመወዝ እና ጥማጥቅም ማስተካከያ መመሪያ ወጥተው ወደ ሥራ እንደገቡም አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀደመው መዋቅር 658 የኀላፊነት ቦታዎች ነበሩት፤ በተሠራው አዲስ መዋቅር እነኝህ የኀላፊነት ቦታዎች ወደ 440 ዝቅ መደረጋቸውም ተጠቁሟል።
አንድም ሠራተኛ ከሥራ ገበታ እንደማይፈናቀል አጽንኦት ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው ጤናማ እና ግልጽ አሠራርን በማጠናከር ከሠራተኞቹ እና ከመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በጋራ በመሥራትም ለተሻለ ስኬት እና ለውጥ እየሠራ እንዳለም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
