
ባሕር ዳር: ኅዳር 9/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጋብቻ መካከል የሚገኝ የንብረት ባለቤትነት መብት እና አሥተዳደር ራሱን የቻለ ሕጋዊ አሠራር ያለው እና መመሪያ የተዘጋጀለት ጉዳይ ነው። በዚህ የሕግ ማዕቀፍ መሠረትም ከሕጉ ያፈነገጠ እና የንብረት ባለቤትነት መብቱን ጥሶ የተገኘ አካል ላይ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልም ተመላክቷል።
ኃይሌ አለነ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸው። በጋብቻ ውስጥ የግል እና የጋራ ንብረትን በተመለከተ የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ ምን እንደሚል ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
ጋብቻን በተመለከተ ክልሎች የየራሳቸው የቤተሰብ ሕግ ያላቸው እንደኾነ ተናግረዋል። በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 79/1995 ከአንቀጽ 13 እስከ 15 በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሠረት ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሃይማኖት እና በባሕል ሥርዓት መሠረት ሊፈጸም ይችላል ብለዋል፡፡
ከተጠቀሱት የጋብቻ መፈጸሚያ ሥርዓቶች ውስጥ በአንደኛው ሥነ ሥርዓት ጋብቻ የተፈጸመ እንደኾነ በጥንዶቹ መካከል ቢያንስ ሦስት በሕግ እውቅና የተሰጣቸው የትዳር ግንኙነት ውጤቶች ይመሠረታሉ ነው ያሉት።
እነዚህም ግላዊ ግንኙነትን የሚመለከት (የመረዳዳት)፣ ንብረትን የሚመለከት እንዲኹም ቀለብ የመስፈር ግዴታዎች ናቸው ይላሉ።
ጥንዶቹ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት የጋብቻ መፈጸሚያ መንገዶች ውስጥ በአንዱ ጋብቻ ቢፈጽሙ የጋብቻ ውጤትን መሠረት በማድረግ በሕግ የጋራ እና የግል ንብረቶቻቸው ላይ የሚኖረው ውጤት ተመሳሳይ ነው ብለዋል፡፡
በመኾኑም በጋብቻ ውስጥ ንብረትን አስመልክቶ የሚኖርን ሕጋዊ ግንኙነት በተለይም የግል ኾነው ሊቀጥሉ የሚችሉና የጋራ የሚኾኑ ንብረቶችን ሕጋዊ የአሥተዳደር ኹኔታ በተመለከተ በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ ተጠቅሷል።
የጋብቻ መመሥረት ከሚፈጥራቸው ሕጋዊ ግንኙነቶች ውስጥ ንብረትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው ይላል ሕጉ።
የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 53 ላይ በመርሕ ደረጃ ተጋቢዎች ንብረታቸውን በተመለከተ ስለሚያስከትለው ውጤት ጋብቻቸውን ከመፈጸማቸው በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸውን በሚፈጽሙበት ዕለት በውል መወሰን እንደሚችሉ ደንግጓል።
በተያያዘ በአንቀጽ 54(1) እና (2) መሠረት በሕግ የተከለከለ ሰው የጋብቻ ውል ለመዋዋል የሕግ ችሎታ ያለው ሲኾን ይህም ውል እርስ በራሱ ሊፈጽመው እና በፍርድ ቤት ሊጸድቅ እንደሚገባም ተመላክቷል ብለዋል የሕግ ጠበቃ እና አማካሪው ኃይሌ አለነ፡፡
የጋብቻ ውል በጽሑፍ መደረግ እና በአራት ምስክሮች (በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን ሁለት) ኾነው ሊፈርሙበት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የባል እና ሚስት የጋራ ሃብትን በተመለከተ ውል ያልተደረገ እንደኾነ ወይም የተደረገው ውል በሕግ ፊት የማይጸና አንደኾነ በሕጉ የተቀመጠው እንደሚከተለው ነው።
በአንቀጽ 73(1) ሥር በተደነገገው መሠረት ባል እና ሚስቱ ከግል ጥረታቸው እና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሃብቶች እንደሚኾኑ በግልጽ ተቀምጧል፡፡
በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 73(2) እንደተጠቀሰው እና በአንቀጽ 69(2) መሠረት የአንደኛው ተጋቢ የግል ሃብት ነው ካልተባለ በስተቀር ባል እና ሚስት ከተጋቡ በኋላ የሚያገኙት ንብረት ሁሉ የጋራ ሃብታቸው ይኾናል የሚል ነው፡፡
እንዲኹም በአንቀጽ 73(3) በስጦታ ውል ወይም በኑዛዜ ቃል በሌላ አኳኋን ካልተመለከተ በስተቀር በስጦታ ወይም በኑዛዜ ለተጋቢዎቹ የተሰጧቸው ንብረቶች ሁሉ የጋራ ሀብቶች እንደሚኾኑም ተደንግጓል።
👉 በጋብቻ ውስጥ የግል ንብረት፤
በሕግ በጸና የጋብቻ ግንኙነት ውስጥ መግባት (በጠባብ ሁኔታም) ቢኾን የግል ንብረት ከማፍራት አይከለክልም። በዚህም ምክንያት በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 68 መሠረት ባል እና ሚስት ጋብቻ በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ፣ በግል ንብረት ለውጥ የተገኘ እና በየግላቸው ያገኟው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ኾነው ይቆጠራሉ በማለት ያስቀምጣል።
በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው ጋብቻ በሚፈጽምበት ጊዜ በግል የነበረው ንብረት ከጋብቻ በኋላም የግል ኾኖ እንደሚቀጥል እና ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ የሚያገኟቸውን ንብረቶች በጋብቻ ውስጥ የግል ኾነው እንደሚቀጥሉ በመርሕ ደረጃ ተደንግጓል፡፡
ይሁንና በጋብቻ ውስጥ በእነዚህ ንብረቶች አማካኝነት የሚገኝ ገቢ ከፍ ብሎ በአንቀፅ 73 ስር በተመለከተው አግባብ የጋራ ሀብት ይኾናል።
ሌላው በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 69(1) መሠረት ባል እና ሚስት ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በኾነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሽጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ይባልልኝ ብሎ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ያጸደቀው እንደኾነ የግል ሀብቱ ይኾናል ይላል ሕጉ፡፡
በመኾኑም በፍቺ ጊዜ ወይም ጋብቻቸው በሚፈርስበት ጊዜ ባል እና ሚስቱ የግል ሀብት መኾኑን በማስረዳት የግል ንብረታቸውን መልሶ የመውሰድ መብት ይኖራቸዋል።
👉 የንብረት አሥተዳደር፤
በአንቀጽ 70(1) መሠረት በመርሕ ደረጃ እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን ራሱ የማሥተዳደር እና ገቢውንም መሰብሰብ ይችላል። የግል ሃብቱ ላይ በነጻነት የማዘዝ ሥልጣንም በአንቀጽ 70(2) ተሰጥቶታል ማለት ነው።
ነገር ግን ይህ ቢኖርም በአንቀጽ 71 (1) መሰረት ባል እና ሚስት አንደኛው የሌላኛውን ተጋቢ የግል ሀብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያሥተዳድርለት እና እንደ አስፈላጊነቱ እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ሕጋዊ የውክልና ሥልጣን አሰጣጥ ሂደትን የሚከተል ይኾናል ብለዋል ጠበቃው።
በጋብቻ ውስጥ ንብረትን በተመለከተ ቀዳሚው ነገር ባል እና ሚስቱ የጋብቻ ውል እንዲያደርጉ በሕጉ የሚጠበቅ ሲኾን ውል ካልፈጸሙ ወይም የፈጸሙት የጋብቻ ውል በሕግ ፊት የማይጸና እንደኾነ በትዳር ውስጥ የሚያፈሯቸው ንብረቶች የግል ወይም የጋራ ናቸው ለማለት የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎች እና የሰበር ውሳኔን መሠረት በማድረግ ይኾናል።
አንድ ጊዜ በሕግ ፊት የሚጸና ትዳር ከተፈፀመ በኋላ በትዳር ውስጥ የሚፈራ ንብረት የግል ስለመኾኑ ካልተገለጸ በቀር ንብረቱ የጋራ ንብረት ተደርጎ የሕግ ግምት እንደሚወሰድ የሕጉ አንቀጽ 74 በግልጽ ይደነግጋል።
👉 የጋራ ንብረትን በተመለከተ የተጋቢዎች ስምምነት አስፈላጊ የሚኾኑባቸው ጉዳዮች፤
ሀ. የጋራ የኾነን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ፤ ለመለወጥ፤ ለማከራየት በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ በዚሁ ንብረት ላይ ሌሎች ሰዎች መብት እንዲያገኙ ለማድረግ፣
ለ. ዋጋቸው ከብር አምሥት መቶ በላይ የኾኑ የሚንቀሳቀሱ የጋራ ንብረቶችን ወይም የገንዘብ ሰነዶችን ለመሸጥ፣ ለመለወጥ በመያዣ ወይም በዋስትና ለመስጠት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ለማስተላለፍ፣
ሐ. ከብር አንድ መቶ በላይ ዋጋ ያለውን የጋራ ንብረት ወይም ገንዘብ ለሌላ ሰው በስጦታ ለማስተላለፍ፣
መ. ከብር 500 በላይ ገንዘብ ለመበደር ወይም ለማበደር ወይም ለሌላ ሰው ዋስ ለመኾን የሌላውን ተጋቢ ፍቃድ ያስፈልጋል።
ከዚህ ውጭ በኾነ መንገድ የሚከናወን ተግባር በሕግ ተቀባይነት እንደሌለውም በሕጉ ላይ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!ሀ
