
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለጤና ባለሙያዎችና ለኅብረተሰቡ የሚያገለግሉ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስ እያመረተ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ክፍል የሚሠሩ መምህራን የኮሮናቫይረስን መከላከል የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ለጤና ባለሙያዎች እያቀረቡ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የሠሯቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ዛሬ ሰኔ 9/2012 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ለዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች አስተዋውቀዋል፡፡
ለጉብኝት ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች መካከል መካኒካል ቬንትሌተር (አጋዥ መተንፈሻ መሳሪያዎች)፣ የሙቀት መለኪያ (ቴርሞ ሜትር) እና ሙሉ በመሉ ፊት ለመሸፈን የሚያስችሉ የጥንቃቄ መጠበቂያ መሳሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሜካኒካል ቬንትሌተር ሥራው 50 በመቶ ድረስ መከናወኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡ የሙቀት መለኪያ መሳሪያው እና ሙሉ በሙሉ ፊት ለመሸፈን የሚያስችለው (ፌስ ሺልድ) ደግሞ አግልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
በሥራው ከ30 እስከ 40 መምህራን እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እየተሳተፉ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን መካከል መምህር ዮሴፍ ብርሃኑ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሃሳብ ያላቸው ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ለሥራ እንዲያውሉ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በዚህም ቴርሞ ሜትር እና ሙሉ በሙሉ የፊት መሸፈኛ በመሥራት ለሃኪሞች ማቅርብ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ክፍል መምህራን የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ጊዜያቸውን በፈጠራ ሥራ እያሳለፉ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶክተር) ዩኒቨርሲቲው በፈጠራ ሥራ ለተሰማሩ መምህራን ድጋፍና ትልቅ እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ዓለምን እያስጨነቀ ለሚገኘው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ሁሉም በሚችለው ልክ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኮሮናቫይረስ ህሙማንን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ የሚከላከሉ አልባሳትን ማምረት መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
