የደቡብ ወሎ ዞን ያሠለጠናቸውን የሰላም አስከባሪ አባላትን በጊምባ ከተማ አስመረቀ።

3

ደሴ: ኅዳር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች የተመለመሉ እና በጊምባ ማሠልጠኛ ማዕከል ለወራት ሥልጠናቸውን የወሰዱ የሰላም አስከባሪ አባላትን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የሰላም አስከባሪ ተመራቂዎች የተሰጣቸው በተግባር የተደገፈ የአካል ብቃት እና የሥነልቦና ግንባታ ሥልጠና የነበራቸውን ወታደራዊ አቅም እና ዕውቀት እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል። የሚሰጣቸውን ማንኛውም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል አባተ ደምሴ በዞኑ የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ኀይልን የመመልመል እና የማሠልጠን ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላቱ በሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት በመጠቀም ሀገር እና ሕዝብ የጣለባቸውን ኀላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ዘለቀ አለባቸው ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት በሥልጠና ላይ እያሉ በዞኑ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመኾን በተግባር የሚገለጥ ሥራ በመሥራታቸው በዞኑ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አድርገዋል ብለዋል።

በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ የተሰጠው ሥልጠና የመጨረሻ ባለመኾኑ ቀጣይነት ያለው የሥራ ላይ ወታደራዊ እና የሥነ ልቦና ግንባታ ሥልጠና እና ልምምድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ተመራቂ አባላቱ የሚገጥሟቸውን ልዩ ልዩ ፈተናዎች ተቋቁመው የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የክልሉን እና የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ እንዲሠሩ አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የክልል የጸጥታ ኀይሎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን ባደረጉት ተጋድሎ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መጥቷል ነው ያሉት።

በዞኑ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የጸጥታ ኀይሉን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የአካባቢውን የጸጥታ ኀይል አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሰላም አስከባሪ ሠልጣኞችን አሠልጥኖ ማስመረቁን አንስተዋል።

ተመራቂዎቹ ክልሉ እና ሀገር ከገጠማቸው ፈተና ለማውጣት የተዘጋጃችሁ የቁርጥ ቀን ልጆች በመኾናቸሁ የተሰጣችሁን ተልዕኮ በብቃት እንደምትወጡ እንተማመናለን ብለዋል።

ዘጋቢ፦አንተነህ ጸጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየውኃ ፖለቲካ፣ የቀይ ባሕር ተዋንያን እና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ
Next article“የብልጽግና ጉዟችን ሁሉንም ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ራዕይ የሚመራ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ