
ከሚሴ: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል
ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች በመጡበት ወረዳ ሰላምን ለማረጋገጥ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
የጥፋት ኀይሎች በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱትን በደል እና ግፍ ማኅበረሰቡ በመገንዘቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን ለመመከት የተሠራው ሥራ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም ካውንስል ሠብሣቢ ዳመነ ታደሰ በተቋቋመው የሰላም ካውንስል በኩል በተደረገው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ከ800 በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎች ወደሰላም እንዲመጡ መደረጉን አስገንዝበዋል።
የሰላም ጥሪው አሁንም የቀጠለ በመኾኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደሰላም እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ በተሠራው የተቀናጀ ሥራ በኹሉም ወረዳዎች ሰላም መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
የልማት ሥራዎችን መከወን የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመኾኑ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ኹሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በቀጣይም ሕግ የማስከበር ተግባሩ በቅንጅት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
