
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን በየዓመቱ ኅዳር 11 ይከበራል፡፡ ቀኑን አስመልክቶ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ“ የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን ይከበራል ብለዋል፡፡ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
ሕጻናት የሀገር የወደፊት ተስፋ እና ሃብት ናቸው፤ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ላይ መሥራት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጅ እና በማኅበራዊ ኑሮ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብት ድንጋጌ አንቀጽ 32 ሕጻናት ከማንኛውም አይነት የኢኮኖሚ ብዝበዛ ፣ ከአካላዊ፣ ማኅበራዊ እና አዕምሯዊ እድገታቸው ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ነገሮች እንዲጠበቁ ተደንግጓል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም አንቀጽ 36 ላይ የሕጻናት መብት እና ደኅንነት መጠበቅ እንዳለበት ይደነግጋል ብለዋል። ሌሎች የሚቀረጹ ፖሊሲዎችም ሕጻናትን ያካተቱ እንዲኾን በሰፊው እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ የወጡ ሕጎች በመተግበራቸው ለውጥ እየመጣ ነው ብለዋል።
የሕጻናትን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ መዋቅር ተዘርግቶ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ተቋማት በሥራቸው የሕጻናትን ጉዳይ አካተው እንዲሠሩ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
በሕጻናት ቀን ሕጻናት ተሰባስበው በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት በመኾኑ በክልሉ ለሁለት ወራት በተለያዩ ሁነቶች እስከ ወረዳ ድረስ ሲከበር ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕጻናት መብት እና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል፡፡
የሕጻናት ፓርላማ የሕጻናትን መብት ማስጠበቂያ በመኾኑ በራሳቸው ፓርላማ እና በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች ለመብቶቻቸው እና ደኅንነታቸው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ከሚዲያዎች ጋር በጋራ እየተሠራ መኾኑንም በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡
የሕጻናት ቀን መከበር ዋና ዓላማ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በሚያወጧቸው ፖሊሲዎች የሕጻናትን ጉዳይ አካተው እንዲፈጸሙ ለማስቻል ያግዛል ነው ያሉት፡፡
በዚህ ዓመት በዓሉ ሲከበር ባለድርሻ አካላት የሕጻናትን መብት በማስከበር ረገድ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ እና የሕጻናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያግዝ ለማስቻል ብለዋል፡፡
“የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” የሚለው መሪ ቃልም በየአካባቢው ላሉ ሕጻናት የመጫወቻ እና መዝናኛ ቦታዎች እንዲመቻቹ ለማድረግ መኾኑን አንስተዋል።
በዓሉን ታሳቢ በማድረግ ከ871 ሺህ በላይ ሕጻናት በየአካባቢያቸው በመጫወቻ ቦታዎች አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በሁሉም አካባቢዎች የሕጻናት ማቆያ እንዲኖር ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ለሚገኙ 272 የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። ለእነዚህም በቁሳቁስ በማጠናከር ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የሕጻናት ድጋፍ እና እንክብካቤ በየቀበሌው በማዘጋጀት ሕጻናትን እና ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ ልጆች ባሕላቸውን እና አካባቢያቸውን ሳይለቁ እንዲያድጉ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ሕጻናት የሀገር ተረካቢ በመኾናቸው ሕጻናት ላይ ዛሬውኑ መሥራት ይገባል ያሉት ኀላፊዋ ሁሉም ለሕጻናት ትኩረት እንዲሰጥም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
