አሚኮ ከዘገባ ሥራዎች ባለፈ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር እየሠራ ነው።

3
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለአጋር ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠና እየሠጠ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ የሥልጠና ማዕከል ዋና ዓላማ ዕውቀት እና ክህሎትን ማዳበር እንደኾነ የተናገሩት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥልጠና እና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተሩ ሐሰን መሐመድ ናቸው። ተግባቦትን ለማጠናከር እና አጋርነትን ለማጎልበት በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል።
ይህንን ዓላማ ለማሳካት በሥልጠና እና ምርምር ማዕከሉ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ እና አዳዲስ የአሠራር ስልቶችን በጥናት እና ምርምር በመለየት ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
ለሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠናውን መስጠት ያስፈለገበት ምክንያትም አሚኮ የተለያዩ መረጃዎችን ከተለያዩ የሕዝብ ግንኙነት ምንጮች ስለሚወስድ ነው ብለዋል።
መረጃ በጥራት እና በሥርዓት መያዝ ስላለበት እና አጋርነትን ለማጠናከር እንዲሁም ጥራት ያለው ዘገባ እንዲቀርብ ለማድረግ ሥልጠናው መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት።
በዚህ ሥልጠና ላይ ብዙ ክፍተቶችን ለይተናል። በተለይ ሥልጠናውን የሚወስዱ ሰልጣኞች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሠሯቸውን ዘገባዎች ጥራት ለማሻሻል ታስቦ የተዘጋጀ እንደኾነም ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ይዘቶች ጥራት ያላቸው እንዲኾኑም አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
የሥልጠና እና ምርምር ማዕከሉን ይበልጥ ለማጠናከር እና ከውጭ ያሉ ደንበኞች እና ተቋማትም ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማድረግ ዕቅድ ስለመኖሩም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ የተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እንደተናገሩት በአሚኮ የሥልጠና እና ምርምር ዳይሬክቶሬት በኩል እየተሰጠን ያለው ሥልጠና ሥራችንን ለማጠናከር እና የመረጃ ልውውጥ ተግባርን የተሻለ ደርጃ ለማድረስ ያግዘናል ብለዋል፡፡
ያሉብንን የአቅም ክፍተቶች ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ በተግባር እንድንሰለጥን ዕድል ፈጥሮልናልም ብለዋል የሥልጠናው ተሳታፊዎች።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሐ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበኩር ጋዜጣ ኅዳር 8/2018 ዓ.ም
Next articleለፖሊስ አባላት የተሰጠው ዕውቅና እና ማበረታቻ የበለጠ ለሥራ የሚያነሳሳ ነው።