
ጎንደር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የትምህርት ሥራን በአዲስ አቅም እና በልዩ ትጋት ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከርእሰ መምህራን እና ከክፍለ ከተማ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ተወዳዳሪ የኾነ እና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ትምህርት ላይ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ በዘርፉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ትምህርትን ቀዳሚ አጀንዳ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ባለፉት ወራት በየደረጃው ያሉ አካላት እና ወላጆች ለተማሪዎች ምዝገባ ጥረት በማድረጋቸው ተማሪዎችን ለማስተማር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመገብ ታቅዶ ሥራ መጀመሩን አንስተዋል።
ምገባ መርሐ ግብሩ 319 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚጠይቅ እንደኾነም ተገልጿል። የተማሪዎች ምገባ መጀመሩንም ተናግረዋል።
የተማሪ ምገባ ለጀመሩ ትምህርት ቤቶችም ምስጋና አቅርበዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ተማሪዎችን ለማብቃት የእርስ በእርስ መማማር ማጠናከር፣ ቤተ መጽሐፍት በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል እና ቤተ ሙከራን ተግባራዊ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ማርታ አዱኛ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
