ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበት የቡሬ ደብረ ማርቆስ ሳብስቴሽን ግንባታ ምን ላይ ነው?

4
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ምንይችል ክንዴ በጣውላ እና ጋራዥ ሥራ የሚተዳደሩ የቡሬ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡
በዚህ ሥራ ከተሰማሩ ረጅም ጊዜ እንዳስቆጠሩ የሚናገሩት አቶ ምንይችል ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ለመሥራት የኤሌክትሪክ ኀይል ማነስ እና መቆራረጥ እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማርካት እና በዕቅዳቸው መሠረት ለመከወን ተግዳሮት እንደኾነባቸው ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
ወደፊት የሚሠራው ሰብስቴሽን ሲጠናቀቅ ያለባቸውን የኤሌክትሪክ ኀይል ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ያስረዳሉ፡፡
ሌላው አሚኮ ያነጋገራቸው የሪች ላንድ ኢንዱስትሪያል ፋብሪካ የምርት ክፍል ኀላፊ ግርማ ሞላ ፋብሪካው በ2016 ዓ.ም ወደ ማምረት ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ዘይት፣ የኬክ ፓውደር እና የእንስሳት መኖ እንደሚያመርትም ተናግረዋል፡፡ ከምርቶቹ ውስጥ አኩሪ አተርን በማቀነባበር የኬክ ፓውደር ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብም ነው ያስረዱት፡፡
ከሁለት ዓመት ጀምሮ ፋብሪካው ሥራ ማቆሙን የተናገሩት ኀላፊው ሥራ ካቆመበት ምክንያቶች አንዱ ፋብሪካውን በሙሉ አቅሙ ማንቀሳቀስ የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት አለመኖር መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለው የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ አይደለም ግማሽ አቅሙን እንኳን ማንቀሳቀስ አያስችልም ነው ያሉት፡፡
ይህንን ጥያቄ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል አቅርበው “በቅርቡ የተቋረጠው የሳብስቴሽን ግንባታ ይጀመራል” ከሚል ምላሽ ውጭ ምንም ዓይነት መፍትሄ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ሌላው በቡሬ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የማሪክ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ማሪክ ኢንዱስትሪያል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2016 ዓ.ም ማሽን በመትከል በአካባቢው ያሉ የበቆሎ ግብዓቶችን በማቀነባበር እስታርች እና የስታርች ውጤቶችን በዋናነት የሚያመርት ነው።
ዱቄት፣ የእንስሳት መኖ እና የቅንጨ ምርት በማምረትም ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሚያቀርብ የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ አስቻለው አዳነ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው በአፍሪካ ከሚገኙ ጥቂት ፋብሪካዎች አንዱ መኾኑን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ ፋብሪካው በቀን እስከ 240 ቶን የማምረት አቅም አለው ብለዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ 40 ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የፈጠረ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ፋብሪካው ከሐምሌ 20/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሙሉ አቅሙ እየሠራ አለመኾኑን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ የኤሌክትሪክ ኀይል ማነስ ትልቅ ችግር እንደኾነባቸውም ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው 24 ሰዓት የመሥራት አቅም ያለው እንደኾነም ጠቁመዋል። አሁን ባለው የኤሌክትሪክ አቅም ግን 4 ሰዓት የሞላ ጊዜ መሥራት እንኳን እንደማይችሉ ነው የተናገሩት፡፡
የኤሌክትሪክ ኀይል ችግሮቹ ቢፈቱ ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ በቆሎን በማቀነባበር እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የቡሬ ደብረማርቆስ ሳብስቴሽን ብዙ የኤሌክትሪክ ኀይል የማመንጨት አቅም ያለው ግንባታ ነው ያሉት የቡሬ ደብረ ማርቆስ ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ገዛኸኝ ካሳሁን ናቸው፡፡
የኀይል ሰብስቴሽን ግንባታው በ9 ነጥብ 1 ሄክታር መሬት የሚያርፍ ግንባታ መኾኑንም ገልጸዋል።
በቲ ዋን የቻይና ፕሮጀክት የሚገነባው ስብስቴሽኑ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ገደማ ሲጀመር በ18 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎም ነበር ብለዋል። ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ግንባታው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የቆየውን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ወደ ሥራ መገባቱንም ሥራ አሥኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ የገባበት ጊዜ ጥሩ ጊዜ ነው ያሉት ሥራ አሥኪያጁ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኀይል መስጫ ሰብስቴሽኑ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ 200 ኪሎ ቮልት የሚኾን ኀይል ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡
ለአካባቢው ነዋሪዎች እና የኤልትሪክ ኀይል ለሚያስፈልጋቸው ተቋማትም ያለባቸውን የኀይል እጥረት ሙሉ በሙሉ ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመሶብ የአንድ አገልግሎት ማዕከል ዜጎች ክብራቸው ተጠብቆ እና ሳይንገላቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው።
Next articleከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመገብ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።