
ደብረማርቆስ: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአፈር ለምነትን እና ምርታማነትን ለማሻሻል ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል።
የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ለማሻሻል ከሚያግዙ ግብዓቶች መካከል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለ2018/19 የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል 10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለማዘጋጀት ታቅዶ የዕቅዱን 98 በመቶ የሚኾነውን ማዘጋጀት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያን ሊተካ የሚችል ጥራቱን የጠበቀ ኮምፖስት በማዘጋጀት ሂደት የሚታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
በዞኑ 86 ሺህ ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
ቨርሚ ኮምፖስት ካለው የአፈር ለምነትን እና ምርታማነትን የማሻሻል ጉልህ ፋይዳ አኳያ ሞዴል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች በስፋት ሊያዘጋጁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ከባዮ ጋዝ የሚመነጨውን ባዮሳለሪ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል እና የመሬትን ምርታማነት ለማሳደግ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
በተያዘው ዓመትም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ22 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ባዮሳለሪ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በዞኑ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል፣ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን በኖራ የማከም ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
