
ወልድያ: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እያካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎች፣ የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ባለሙያዎች፣ የሰሜን ወሎ ዞን፣ የቆቦ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ባለሙያዎች፣ የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች በቆቦ ከተማ የተዘራ የመልካም ማሽላ ዘር ብዜትን ጎብኝተዋል።
በማሳቸው ላይ መልካም ማሽላ የዘሩ አርሶ አደሮች ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት በጤፍ፣ በስንዴ እና በማሽላ የምርጥ ዘር ብዜት ልዩ ልዩ ፍጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርግላቸው ድጋፍ ያመሠገኑት አርሶ አደሮቹ ዘር ሠብሥበው ለማኅበራት ከሚያስረክቡ ይልቅ በዘር አምራች ተደራጅተው ለሌሎች አርሶአደሮች የማሰራጨት ፍላጎት እንዳላቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።
በማኅበር መደራጀታቸው ከዘር እስከ ሠብል ሥብሠባ ያሉትን ሂደቶች በእርሻ ሜካናይዜሽን ለመሥራት አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ነው የገለጹት።
የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ስዩም አሰፌ (ዶ.ር) ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት ስኬታማ የዘር ብዜት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከዘር አቅርቦት ጀምሮ ሙያዊ እገዛ በማድረግ ውጤታማ ዘር ለማመንጨት በትኩረት መሥራቱን ይቀጥላል ነው ያሉት።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ቢሆን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በማሽላ፣ በጤፍ፣ በስንዴ እና በድንች ዘር ብዜት ላይ በማተኮር በቆቦ ከተማ፣ በሀብሩ፣ በጋዞ እና በዋድላ ወረዳዎች በ53 ሄክታር መሬት ላይ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የዘር አቅርቦት፣ የባለሙያ እና የአርሶ አደሮች ሥልጠና፣ የማሳ ላይ ክትትል እና ድጋፍ ማድረጉንም አስረድተዋል።
ምርጥ ዘር አምራች አርሶ አደሮችን በማደራጀት አቅማቸው እንዲጎለብት ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው እየሠራ መኾኑንም ለአሚኮ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
