“የዓባይ ግድብን ላሳካን ሕዝቦች የባሕር በር የማግኘታችን ጉዳይ ምንም ነው” ፕሮፌሰር አደም ካሚል

3
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ተጠቃሚነት ታሪክ የመዘገባት ዛሬ ሳይኾን ቀደም ብሎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የቀደሙ ሥልጣኔዎች ሲነሱ አብሯቸው የሚነሳውም ቀይ ባሕር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ታሪኳ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ቁርኝት የይስሙላ ብቻ ሳይኾን ቀይ ባሕር ራሱ ቀይ ባሕር የሚለውን ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት “ባሕረ ነጃሺ” ወይም “የሐበሻ ባሕር” ይባል እንደነበረ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ይገልጻሉ፡፡
አክሱም ላይ ኾነው ኢትዮጵያን (ሐበሻን) ያሥተዳደሩ ነገሥታት በሙሉ ”ነጃሺ” ይባሉ እንደነበረ ያስታወሱት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በወቅቱ የቀይ ባሕር ስያሜም ባሕረ ነጃሺ ወይም የሐበሻ ባሕር ይባል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ዕድገት፣ እምነት እና ንግዷ ጭምር የተሳሰረው ከቀይ ባሕር ጋር መኾኑን ያነሱት የታሪክ ምሁሩ በወቅቱ በቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚገኘው የአዶሊስ ወደብ የኢትዮጵያዊያን የንግድ ማሳለጫ እንደነበረም አንስተዋል፡፡
በአክሱም የነገሡት የሐበሻ ንጉሦች ቀይ ባሕርን በመቆጣጠር እና በማሥተዳደር በዚያ አካባቢ ለሚፈጠሩ ውዝግቦች እና አለመግባባቶች ሽምግልና ሲሰጡ የነበሩት ቀይ ባሕር የራሳቸው ንብረት በመኾኑ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር አደም ካሚል፡፡
የኢትዮጵያውያን አሻራ፣ እምነትም ኾነ ሥልጣኔ ከቀይ ባሕር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው የሚሉት የታሪክ ምሁሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ570 ዓመተ ዓለም የአይሁድ እምነት ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቀይ ባሕርን ተሻግሮ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የእስልምና ሃይማኖትም በ615 በመካ ተወልዶ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በሐበሻ ምድር መሠረቱን ስለመጣሉም ገልጸውልናል፡፡
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ ወይም በቀይ ባሕር እንዳትጠቀም ከሚፈልጉት ሀገራት መካከል ግብጽ ቀዳሚዋ ስለመኾኗ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ማስረጃዎችን ዋቢ አድርገው ይገልጻሉ፡፡
ፈርኦኖቹ ኢትዮጵያውያን በናይል ወይም ዓባይ ወንዝ እንዳንጠቀም ባደረጉት ጥረት ልክ በቀይ ባሕርም እንዳንጠቀም በመጣር ላይ ይገኛሉ ያሉት ኘሮፌሰሩ የኢትዮጵያ እድገት ሁሌም ለግብጻውያኑ ውድቀታቸው መስሎ ይሰማቸዋል ሲሉም ምክንያታቸውን አቅርበዋል፡፡
በኛ ውኃ የተመረተ የጥጥ ምርት ለእንግሊዛውያኑ የዘውድ አገዛዞች (ለንግሥት ቪክቶሪያ) በመላክ የሚጀምረው የግብጻውያኑ ክፋት ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ምንም ነገር እንዳትጠቀም ለማድረግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋቸውንም የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል፡፡
የግብጽ መሪዎች አጼ ቴዎድሮስ በእንግሊዛውያን እንዲገደሉ ማድረግን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለንተናዊ መዳከም ውስጥ እንዲገባ ከጥንት ጀምሮ ጥረት ያደርጉ እንደነበርም ኘሮፌሰሩ አንስተዋል፡፡
ግብጻውያን በዘመነ ሙርሲ መሪነት ወቅት በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈጸሙ ዘንድ አራት ውሳኔዎችን ወስነው ነበር፤ እነዚህ አራት ውሳኔዎች ከኢትዮጵያ ጋር የተኳረፈችውን ኤርትራን በማስታጠቅ ውጊያ ማስጀመር፣ ጅቡቲ የአረብ ሊግ አባል ስለኾነች ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንድታቆም ማድረግ፣ ሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲ የተባሉት ኢትዮጵያዊ ባለሃብት የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው በመኾኑ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ለማድረግ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር መነጋገር እና የኦጋዴን ታጣቂዎችን በመሣሪያ በመደገፍ በኢትዮጵያ ግጭት እንዲፈጥሩ ማስቻል የሚሉ እንደነበሩ ኘሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡
የግብጽ መንግሥት በኤርትራ ራስ ገዝ መኾን ወይም ከኢትዮጵያ መገንጠል ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን በደማቁ ስለማሳረፋቸውም ኘሮፌሰር አደም ይጠቅሳሉ፡፡
አብዛኛው ኤርትራዊ ከኢትዮጵያ የመነጠል ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በተገነጠለችበት ወቅት የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከዚያም ቀጥሎ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ቡትሮስ ጋሊ በኤርትራ መገንጠል እና በኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት ውስጥ አሻራቸውን ካሳረፉ ግብጻዊ ፖለቲከኞች መካከል ስለመኾናቸውም አንስተዋል፡፡
የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቅ የሚመሯቸውን ኤርትራውያን ሕይዎት ከመቀየር ይልቅ ለጦርነት በማሠልጠን በአንድ ወቅት ኤርትራ ከዓለም ሀገራት በወታደር ብዛት ስምንተኛ እንድትኾን እስከማድረግ ደርሰዋል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል፡፡ ኤርትራ በርካታ መዋዕለ ንዋይዋን የምታፈሰውም ለጦርነት ዝግጅት በማድረግ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
በየመን፣ በጅቡቲ እና አካባቢዎቹ የባሕር ላይ ውንብድና ለመስፋፋቱ የኤርትራ ደካማ አሥተዳደር ተወቃሽ ነው ያሉት ኘሮፌሰር አደም ካሚል የኤርትራ መንግሥት በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በየመን እና በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት መክፈታቸው ኤርትራን የሚያሥተዳድራት ጦረኛ መንግሥት እንጂ ለሕዝቧ የቆመ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ላለመኾኑ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡
የገልፍ ሀገራት በኤርትራ ላይ ቅሬታ ለማሰማታቸው ምክንያታቸው የቀይ ባሕር ሰላም በመጥፋቱ ነው ያሉት የታሪክ ምሁሩ ቀይ ባሕር በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር በነበረበት ወቅት ሰላሙን እንዳላጣ እና ኢትዮጵያ ከባሕሩ በራቀችባቸው ዓመታት ግን ቀጣናው ሰላሙን በማጣቱ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በብዙ አመክንዮዎች የዓለም ሀገራትን የሚያሳምን ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለ አግባብ ያጣችውን ቀይ ባሕር የማስመለስ እንጂ የጦርነት ፍላጎት ያላት ሀገር አይደለችም ያሉት ኘሮፌሰር አደም ካሚል ኤርትራም ብትኾን ቀይ ባሕር ለሚገባት ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን በማስጠቀም የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ማሳደግ እንደሚገባት አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባልተገባ የፖለቲካ ሸፍጥ እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባልተከተለ መልኩ የባሕር በር እንድታጣ ተደርጋለች፡፡ የራሷ የኾነ የባሕር በር የነበራት ሀገራችን በቅርቧ ካለው ቀይ ባሕር እንዳትጠቀም ወይም የበይዎች ተመልካች እንድትኾን ግድ ተብላለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ትውልዱ ደግሞ በባሕር በር አጠቃቀም ዙሪያ ሀገራችን ላይ ያጠላባትን ጥቁር መጋረጃ በሰላማዊ መንገድ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲቀደድላቸው ይፈልጋሉ ፡፡
የታሪክ ምሁሩ ኘሮፌሰር አደም ካሚልም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ማግኘት መብታቸው እንደኾነ ታሪክን እማኝ እያደረጉ ገልጸውልናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዚህ ድል እንድንበቃ ግን ከመንግሥት ጠንካራ የዲኘሎማሲ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ፣ ሕዝቡ የቀይ ባሕር ጉዳይ የመንግሥት ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የራሱም ጉዳይ እንደኾነ አስቦ በዓባይ ግድብ ላይ ያደረገውን ርብርብ በዚህም ላይ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሃይማኖት፣ በብሔር እና በዘር መከፋፈል እንደማያስፈልግ፣ በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገዶች መፈታት እንዳለባቸው እና የኢትዮጵያውያን አንድነት መመለስ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ግብጻውያን የዓባይ ጉዳይ ከእጃቸው ሲወጣ ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ በውጭ ሀገራት ለኢንቨስትመንት የምትመረጥ ሀገር እንዳትኾን ብዙ ሥራዎችን ይሠራሉ ብለው እንደሚገምቱ የገለጹት ኘሮፌሰሩ ከዚህ ችግር ለመውጣት እና የኛ የነበረውን ቀይ ባሕር ወደኛ ለመመለስ ከምንም በቀደመ ኹኔታ የውስጥ ሰላማችንን መመለስ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ማሳየት ቅንጦት ወይም ጠብ አጫሪነት ሳይኾን ለሀገር እና ለሕዝብ እድገት ነገን ታሳቢ ያደረገ ትልም መተለም ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንም እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ስንቆም አድዋን እና የሕዳሴውን ግድብ የመሳሰሉ ደማቅ ታሪኮች ጽፈናል ብለዋል፡፡ “የዓባይን ግድብ ያሳካን ሕዝቦች የባሕር በር ማግኘታችን ጉዳይ ኢምንት” ነው፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለመማር የሚታትሩ ተማሪዎች እና ለማስተማር የሚተጉ መምህራን ትምህርትን በውጤት ያጅባሉ።
Next articleዘር አምራች አርሶ አደሮችን በማኅበር ለማደራጀት እየሠራ መኾኑን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።