
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “እንኳንስ ሌሎች እኔ አንደኛ ደረጃ ስወጣ እና ስሸለም የከረምኩትም አላለፍሁም” ይህን የነገረን የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የነበረው ተማሪ ብርሃኑ አለልኝ ነው። በ2017 ዓ.ም በትምህርት ቤቱ ሲማሩ ከከረሙት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ አንዳቸውም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችላቸውን ውጤት አላስመዘገቡም ነው ያለው ተማሪ ብርሃኑ።
ይህ የውጤት ቀውስ የተፈጠረው በተማሪ ብርሃኑ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይኾን በሀገሪቱ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መኾኑን ሁላችንም እናስታውሳለን።
ያለፈው የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የውጤት ቀውስ እሱን እና ሌሎች ተማሪዎችንም እንዴት እንደገጠማቸው እና በ2018 ዓ.ም ተፈታኞች ላይም እንዳይደገም ከወዲሁ መደረግ ያለባቸውን ዝግጁነቶች ለመጠየቅ ነው ብርሃኑን ያገኘነው።
“ለብሔራዊ ፈተና ሊመጣ በሚችለው ጥያቄ ልክ ቀድሜ ከመዘጋጀት ይልቅ ቀለል ባሉ የክፍል ፈተናዎች ላይ ጊዜዬን ማጥፋቴ ነው የጎዳኝ” ብሏል ተማሪው።
የትምህርት ፍላጎት ኖሯቸው የሚታትሩ ተማሪዎች ቢኖሩም ክፍል መቁጠር እና ካርዱን ብቻ የሚፈልጉትም ቁጥራቸው ቀላል እንዳልነበር መታዘቡን ገልጿል።
በርካታ ነገሮች በትምህርት ፍላጎትና ታታሪነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ አንስቷል። በተለይም ብሔራዊ ፈተናው እንደሚከብድ እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እንደማይቻል ቀድሞ የሚናፈስ ወሬ ሥነ ልቦናን ይረብሻል፤ የትምህርት ፍላጎትንም ይቀንሳል ነው ያለው። የፍላጎት ማጣት ደግሞ የውጤት መውረድ ዋና ምክንያት ነው ብሏል።
ቀጣይ ተፈታኞች አልባሌ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው እና ለዕውቀት ዋጋ በመሥጠት ያለፉ ጥያቄዎችን ቀድመው ማየት እና መዘጋጀት እንዳለባቸውም መክሯል። መምህራንም ከፍ ያሉ ጥያቄዎችን በማውጣት ለተማሪዎቻቸው መስጠት እና አብረው እየሠሩ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግሯል።
ተማሪዎች ሲማሩ ከርመው፣ መምህራን በየትምህርት አይነቱ እየተፈራረቁ ሲያስተምሩ ባጅተው፣ ወላጆችም የልጆቻቸውን ነገ ማሳመር በመፈለግ ከሌላቸው ላይ እየቀነሱ ለትምህርት ቁሳቁስ ወጭ አድርገው፣ ነገር ግን አንድም ተማሪ ወደ ቀጣዩ የትምህርት ምዕራፍ ሳያልፍ ሲቀር ከማን ምን ጎድሎ ይኾን ? ብለን ሁላችንም ልናስብበት ግድ ይላል።
በመንግሥት በኩል አስፈላጊው የትምህርት ግብዓት ወይም የመማር ማስተማር ሥርዓት ስላልተዘረጋ ነው? ወይስ ከተማሪዎች እና መምህራን ነው ችግሩ?
የትምህርት ቁሳቁስ እና ግብዓት ችግር ያለባቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸው የታወቀ ነው። ነገር ግን ቀደምት የቀለም ቀንድ ኢትዮጵያውያን የትምህርት ቤት በር ናፍቀው፣ ኪሎ ሜትሮችን በእግር ተጉዘው፣ ከዚያ ዘመን ውስብስብ ችግሮችም በላይ ኾነው፣ እና ዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው ጭምር ታሪክ መሥራታቸውን ስለምናስታውስ “የግብዓት ችግር” ለእንዲህ አይነቱ የከፋ የውጤት ቀውስ ሰበብነቱ ዋነኛ ምክንያት ይኾን ?
ተማሪዎች በታታሪነት ሲማሩ እና መምህራንም በትጋት ሲያስተምሩ ከርመው እንዲህ ያለ ያሽቆለቆለ ውጤት ከመጣ ችግሩ ከወዴት መነጨ ብሎ መጠየቅ የሁሉም ኀላፊነት ነው።
“ትምህርት ለነገ የተሻለ ሕይወት መዘጋጃ ብቻ ሳይኾን የዛሬ ሕይወትም ነው” ይላል እውቁ አሜሪካዊ የሥነ ልቦና ባለሙያ ጆን ዲዊ። እውነት ነው፤ የትምህርት ቤት ቆይታ በፍላጎት፣ በታታሪነት እና በውጤት ሲታጀብ ለነገ መሠረት ነው፤ ለዛሬም የሚኖሩት የተማሪነት ጣፋጭ ሕይወት ነው። ይህ የሚኾነው ግን የተሻለ ትምህርት፣ ዕውቀት እና በወጉ የተለወጠ ባሕሪ ሲኖር ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አማካሪ ካሳሁን አዳነ ትምህርት በዕውቀት እና በሥነ ምግባር መበልጸጊያ፣ የሀገርም መገንቢያ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በዓለም ፊት ተወዳዳሪ እንደኾኑ እና በተለይም አማራ ክልል ደግሞ የቀለም ቀንድ ተማሪዎች መፍለቂያ ከኾኑ አካባቢዎች አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
“መማር ማለት ትምህርት ቤት መሄድና መምጣት ሳይኾን አዲዲስ ነገሮችን ማወቅ እና የባሕሪም ለውጥ ማምጣት ማለት ነው” የሚሉት አማካሪው አሁን ላይ በተለይም በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ የሚታየው የውጤት ማሽቆልቆል የብዙ ተማሪዎች ችግር እየኾነ መምጣቱን አብራርተዋል።
አብዛኛው ሰው የብሔራዊ ፈተናዎችን ውጤት ሲያይ ብቻ ነው ስለትምህርት ጥራት የሚያስታውሰው፤ ነገር ግን በክፍል ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችን ለማለፍም የሚቸገሩ ተማሪዎች እየተበራከቱ ነው ብለዋል።
በቅድሚያ ትምህርት ለሁሉም ነገር መሰረት መኾኑን በማመን በትጋትና ወኔ ትምህርት ቤት መገኘት ግድ እንደሚል አንስተዋል። መንግሥት ምንም ያህል የትምህርት ግብዓቶችን ሊያቀርብ ቢችል እና በየትኛውም ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ቢገነባም የተማሪዎች የመማር ፍላጎት እና የመምህራን ትጋት ካልተጨመረበት ውጤት እንደማይኖረው አስረድተዋል።
የሀገር እና የትውልድ ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በትምህርት ነው፤ ተማሪዎች ይህንን በመረዳት እና አሁን ከሚያጋጥሟቸው አላፊ ችግሮች በላይ ኾነው ነገን በማሰብ ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ እንዲስተጓጎል የሚፈልጉ አካላት በገጠሙ ጊዜም በተለይም እድሜያቸው የሚፈቅድላቸው ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በመኾን መመካከር እና ችግሮች ተፈትተው ለመማር መጣር ነው ያለባቸው ብለዋል። በቀላሉ ተሥፋ መቁረጥ እና ትምህርትን ችላ ማለት፣ አለፍ ሲልም ከቀየ ርቆ በመጓዝ ለነገ ሕይወት በማይበጅ ተግባር መሰማራት እንደሌለባቸውም ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ወይም ደግሞ በሥራ ላይ ኾነውም ውጤት ሲርቃቸው ተማሪዎች ዕውቀታቸውን ብቻ አይደለም የሚቀሙት፤ ሥነ ልቦናቸው፣ እድሜያቸው፣ ሕልማቸው እና የቤተሰቦቻቸው ምኞት ጭምር ነው ጥያቄ ውስጥ የሚወድቀው ብለዋል አማካሪው። በመኾኑም ተማሪዎች ከመሰናክሎች በላይ ኾነው በመበርታት ትምህርት ቤት መገኘት እና በትጋት እና በፍላጎት መማር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
“መምህራን የተማሪዎች የመጀመሪያ ጠበቃዎች እና ፈጥኖ ደራሾች ናቸው” ያሉት አማካሪው በሥነ ልቦና የተጎዱ እና የትምህርት ፍላጎታቸው የቀነሱ ተማሪዎችን በመደገፍ ለውጤት ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
መምህራን ተማሪዎቻቸውን እንደየፍላጎታቸው፣ አቅማቸው፣ የሥነ ልቦና ዝግጅታቸው እና የሚደርሱባቸውን ተጽእኖዎች በመለየት ቀርቦ ማወያየት፣ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ማማከር እና በታታሪነት ተምረው ለውጤት እንዲበቁ የማገዝ ታሪካዊ ኀላፊነት ወድቆባቸዋልም ብለዋል።
ከወቅታዊ ሁኔታዎች በላይ ነገን በማለም ለመማር በቂ ዝግጅት ያለው ተማሪ እና ለማስተማር የሚታትር መምህር ሲገናኙ ትምህርት ይሰምራል፤ ውጤትም ይመዘገባል ነው ያሉት።
ይህ ካልኾነ ግን የተማሪዎችም ኾነ የመምህራን በትምህርት ቤት መገኘት ብቻውን የሚጠበቀውን ውጤት እንደማያስገኝ ገልጸዋል።
ለማስተማር የሚተጋ መምህር እያለ የተማሪው የመማር ፍላጎት ከቀነሰ ትምህርት ውጤታማ አይኾንም፤
ለመማር ፍላጎት ኖሮት የሚታትር ተማሪ እያለ ለማስተማር የማይተጋ መምህር ሲገጥምም እንዲሁ ነው ብለዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለመምህራን የማትጊያ ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚያደርግ፣ መምህራንም ችግሮችን ሁሉ ተጋፍጠው እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል። ለዚህም ትምህርት ቢሮው ምስጋና አለው ብለዋል። ተማሪዎችም ያለትምህርት የሚቀየር ማኅበረሰብ እና ሀገር እንደሌለ አውቀው በትምህርት ቤቶች መገኘት፣ በትጋት መማር እና ለውጤት መብቃት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
