ወሳኞቹ የእርግዝና ወራት የትኞቹ ናቸው?

8
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ልጆች ጤነኛ እና የዳበረ አካል እና አዕምሮ ኖሯቸው ለማደግ ከመጀመሪያዋ የጽንሰት ቀን ጀምሮ እስከ ሦስት ወራት ድረስ የተለየ ትኩረት እና የሕክምና ክትትል ያስፈልጋል።
የውስጥ ደዌ ክሊኒክ ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ብሩክታዊት አሰጌ የእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ልዩ ትኩረትን የሚሹ ናቸው ይላሉ። ምክንያቱም በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የጽንሱ የሰውነት ክፍሎች የሚፈጠሩበት ጊዜ ነው።
ይህ ከስድስት እስከ 13 ሳምንታት ያለው የእርግዝና ወቅት የአካል ግንባታ ጊዜ በመባል ይጠራል ብለዋል ዶክተር ብሩክታዊት አሰጌ።
የነርቭ ሥርዓት፣ የጀርባ አጥንት፣ ልብ፣ የፊት ገጽ፣ ዐይን፣ እጅ እና እግር በእነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሚሠሩ ናቸው።
በመኾኑም በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ለጽንስ እና ለእናት ልዩ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል። እናትም በእርግዝና ወቅት ራሷን ከተለያዩ ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
በዚህ ወቅት እናቶች የተለያዩ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ለውጥ እንደሚያስተናግዱ እና የሕመም ስሜት እንደሚያጋጥማቸውም ሐኪሟ አብራርተዋል።
ቀለል ያለ ራስ ምታት ወይም የማዞር ስሜት፣ ድድ አካባቢ መድማት፣ ትንፋሽ መቆራረጥ፣ የድካም እና የእንቅልፍ ስሜት፣ ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ ጨጓራ ማቃጠል፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ እንዲሁም ጡት አካባቢ ማሳከክ ወይም እብጠት እንደሚከሰትም አስረድተዋል።
እነዚህ ምልክቶች ግን በሁሉም እናቶች ላይ ይታያሉ ማለት እንዳልኾነ አብራርተዋል።
ነፍሰ ጡር እናት ማርገዟን እንዳወቀች ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ የደም፣ የሽንት እና የዘረመል ምርመራ ማድረግ እና ክትትሏን መጀመር እንዳለባትም መክረዋል።
ነፍሰጡሯ እናት ከዚህ ቀደም በሥነተዋልዶ ጤና ዙርያ የነበራት ታሪክ ካለ በዚያ ላይ መሠረት በማድረግ ህክምና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
👉 እርግዝና እንደተፈጠረ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ያለው ጥቅም ምንድን ነው?
ሁሉም እርግዝና ማኅፀን ውስጥ ላይፈጠር ይችላል። የተፈጠረው እርግዝና ከማኅፀን ውጭ ከኾነ እናት የከፋ ጉዳት ስለሚደርስባት ፈጥኖ ወደ ሕክምና መሄድ የእናትን ሕይዎት ያተርፋል።
ጽንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል እናት የምትጠቀመው መድኃኒት ካለም ሙድኃኒቱ እንዲቀየር ወይም እንዲቀር ውሳኔ ለመስጠትም ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
ዶክተር ብሩክታዊት አሰጌ ወደ ሕክምና አበክሮ መሄድ ሌላው ጥቅሙ የእናት አመጋገብ እንዲስተካከል ምክር ስለሚሰጥ የጽንሱ አፈጣጠር ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት።
አንዲት አናት በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሦስት ወራት ወቅት የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የበሰሉ ምግቦችን ብቻ መመገብ፣ የግል እና የአካባቢን ጽዳት መጠበቅ፣ እና ቀለል ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልጋትም ባለሙያዋ መክረዋል።
ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የተለየ ጉዳት ከሚያስከትሉ ድርጊቶች ውስጥ ደግሞ ባለሙያ ሳያማክሩ መድኃኒት መውሰድ፣ ዕፆችን መጠቀም፣ የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ፣ ጫት፣ ከጨረር ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ መሥራት፣ ከፍተኛ የኾነ ሙቀት ያለበት እንደ ስቲም እና ሳውና ባዝ መጠቀም ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል ዶክተር ብሩክታዊት።
እነዚህ ድርጊቶች በጽንሱ ላይ የአፈጣጠር ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
ለእናትም ኾነ ለጽንስ ደኅንነት የሚበጀው ነገር አዘውትሮ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እና ሐኪም ማማከር መኾኑን ዶክተር ብሩክታዊት መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሀቋን ትጠይቃለች፣ የነበራትን ታስመልሳለች”
Next articleየአማራ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት 120 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርቧል።