
ባሕር ዳር: ኅዳር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጠየቀችው የነበራትን፣ ሥልጣኔዋ ያበበበትን፤ ገናና የኾነችበትን ነው። ቀይ ባሕር መስታውት ነው። የኢትዮጵያ መልክ የሚገለጥበት፤ ቀይ ባሕር ጮራ ነው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የበራበት፤ ቀይ ባሕር ጎዳና ነው ወጪ ወራጁ የተመላለሰበት፤ ቀይ ባሕር ምሽግ ነው የኢትዮጵያ ደኅንነት የሚጠበቅበት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚከበርበት፤ የኢትዮጵያ ታላቅነት የተሠራበት፤ የሚሠራበት።
ምንም እንኳን ዛሬ ከኢትዮጵያ የራቀ ቢመስልም፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ሀቅ እንደነበር እንኳን ታሪክ ተናጋሪዎች፤ እንኳን የታሪክ ኪታቦች አንደበታቸው የማይናገረው፤ እጃቸው ታሪክ የማይጽፈው ግመሎች ያውቁታል።
ኢትዮጵያ ታሪኳ ከታሪኩ የተሳሰረ ነውና ሀቋን ትጠይቃለች፤ ሥልጣኔዋ በእርሱ ላይ የተመሠረተ ነውና የሚገባትን ትጠይቃለች።
እድገቷን ለማፋጠን፣ ደኅንነቷን በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ በቀጣናው ያላትን ወሳኝነት ከፍ ለማድረግ የባሕር በር ማግኘት ግድ ይላታል። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በቀጣናው ያለውን የደኅንነት ስጋት ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አስተማማኝ ሰላምም ለመፍጠር የባሕር በር ያስፈልጋል፤ ይገባታልም። ጠላቶች የሚበዙባት ሀገር ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ርቃ መኖር አትችልም።
ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት ?” በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ ብቸኛ መውጪያ እና መግቢያ የባሕር በሯ ከመዘጋት በተጨማሪ ሉዐላዊነቷ ለአደጋ ሊጋለጥ በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ይላሉ።
እጅግ ስትራቴጂክ ከኾነው ከቀይ ባሕር አካባቢ በመገለልዋ በአካባቢው ያላት ተሰሚነት እና ክብር ከባሕር በሮቿ ጋር ሄደዋል፡፡ በርካታ ሀገራትም የቀይ ባሕር ተቀናቃኛቸው የነበረችው ኢትዮጵያን ከባሕሩ አካባቢ አግልለው ቀይ ባሕርን በብቸኝነት ለመጠቀም ሲሠሩ ኖረዋል። ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የደኅንነት ጉዳይ ነው ብለው ጽፈዋል።
ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ሲባል የባሕር ክልሏን ማግኘት ግድ ይላታል። በቀይ ባሕር የኑክሌር መሣሪያ ቢጠመድበት፣ የጠላት ጦር ቢሰፍርበት እና ለኢትዮጵያ ለሕልውናዋ ሥጋት የሚፈጥር ሁኔታ ቢጠነሰስባት ይህንን ለመከላከል ኢትዮጵያ ልታደርገው የምትችል ምንም ነገር አይኖርም ነው የሚሉት።
ለምን ቢሉ አሁን ላይ ቀይ ባሕር የላትምና። ስለዚህ ቀይ ባሕርን ማግኘት ቅንጦት አይደለም። ግዴታ እና የሕልውና ጉዳይ ነው እንጂ።
ኢትዮጵያ በድንበር ዘለል ወንዞችዋ፤ በታሪካዊ እና በጄኦፖለቲካዊ ምክንያቶች በአንዳንድ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በጠላትነት የተፈረጀች ሀገር ናት፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳልተኙላት ሁሉ አሁንም፣ ወደፊትም እንደማይተኙላት በገቢር አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ኖሯት ካልተቋቋመቻቸው በስተቅር የታሪክ ጠላቶቿ በባሕር በር በኩል ገብተው ነው የሚያጠቋት ነው የሚሉት።
የባሕር በር ከኢኮኖሚው ጠቀሜታ ይልቅ የሀገርን ነጻነት እና ደኅንነት ከማረጋገጥ አንጻር የሚኖረው ሚና የላቀ ነው፡፡ የባሕር በር የሕልውና ጥያቄ ነውና ይላሉ።
በባሕር በኩል አድርጎ የሚመጣን ወራሪ ኃይል ለመመከት እና እዚያው በባሕሩ ውስጥ ማስቀረት ከመሬት ውጊያ በጣም የቀለለ ነው።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጠላቶችዋ በቀይ ባሕር በሚገኙ የባሕር በሮች በኩል አድርገው ጦርነት ከፍተውባታል። ይህን ለመከላከል ደግሞ የባሕር በር ማግኘት የመኖር እና ያለመኖር ጉዳይ ነው።
ያዕቆብ ኃይለማርያም(ዶ.ር) ሲጽፉ “ለአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ የሚቀርበው ግልጽ ጥያቄ ኢትዮጵያ ወዳብ አልባ ኾና ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ፣ ባሕሏ የደበዘዘ፣ ፓለቲካዋ የተናጋ ኾኖ ትቀጥላለች ወይስ የባሕር በር ኖሯት ጥንት እንደነበርችው የጎለበተች እና የበለጸገች ትኾናለች ? መልሱ አስቸኳይ ነው፡፡
ምክንያቱም በኮሰሰች እና በደበዘዘች ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ የለምና” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በዓባይ ውኃ ላይ ሲደርስባቸው የነበረውን ውርጅብኝ ተቋቁመው ድል እንዳደረጉ ሁሉ የባሕር በርንም ማግኘት በአንድነት፣ በጀግንነት እና በቁርጠኝነት መጽናት ይገባቸዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባል ኮሞዶር ጥላሁን መኮንን ቀደም ሲል የባሕር ክልል እና የባሕር በር የነበራት ሀገር አሁን ላይ ሁሉንም አጥታለች ነው የሚሉት።
የባሕር ክልል ከኢኮኖሚ ባሻገር ለሀገር ደኅንነት እና ሉዓላዊነት ወሳኝ ነው፤ ሰፊ የባሕር ክልል የነበራት ኢትዮጵያ በባሕር ክልሏ አማካኝነት ደኅንነቷን ስታስጠብቅ ኖራለች፤ ከዓመታት ወዲህ ግን ደኅንነቷን ስታስጠብቅበት፣ ኢኮኖሚያዋን ስታሳድግበት የኖረችውን አጥታለች ይላሉ።
የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል በባሕር በኩል የሚመጣን አደጋ ለመቆጣጠር የተቋቋመ፣ ያንም ሲያደርግ የኖረ ነው። ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ በቀይ ባሕር ብቻ ሳይኾን ከዚያም እየተሻገረች ጥቅሟን ስታስከብር ኖራለች ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያ በባሕር አማካኝነት በሌሎች ሀገራትም እያለፈች ሰላምን ስታስከብር የኖረች ሀገር ናት። የባሕር በር ለኢትዮጵያ የታሪኳ አንድ አካል ነው። ኢትዮጵያ ባሕሯን በማጣቷ ብዙ ነገር አጥታለች፤ ይህ ደግሞ ጎድቷታል ይላሉ።
የባሕር ክልል እና በር ማጣት ያስቆጫል፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የጠየቅችው ጥያቄ ተገቢ ነው፤ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና መልካምድራዊ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምስጢርን ለመጠበቅ፣ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ የባሕር በሯ እና ክልሏ ያስፈልጓታል ነው የሚሉት። ሌላው ቢቀር አሰብ የማንም አይደለም። የኢትዮጵያ ነው ይላሉ።
የባሕር በርን ለማግኘት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚገባም አንስተዋል። የባሕር በርን እና ክልልን ለማግኘት በዲፕሎማሲ ጫና መፍጠር፣ የኢትዮጵያን እውነት ማስረዳት እና ጥያቄዋ መልስ እንዲያገኝ ግፊት እንዲያደርጉ ማድረግ አለባት ነው የሚሉት። በተለይም ታላላቆቹ ሀገራት የኢትዮጵያን ሕጋዊ እና ታሪካዊ ጥያቄ እንዲረዱ ተደጋጋሚ እና ተከታታይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ጥቅሟን አጥታ፤ ደኅንነቷን አጋልጣ፣ የበይ ተመልካች ኾና መኖር አትችልም። ሀቋን የመጠየቅ መብት አላትና። የነበራትንም ማስመለስ ትችላለችና።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
