
ፍኖተ ሰላም: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት መምሪያ በሪፎርም ተግባራት ዙሪያ የአንደኛ ሩብ ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ ከዞን መሪዎች እና ሠራተኞች ጋር አካሄዷል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ተቋማት ለመፍጠር እየተሠራ ነው።
በተለይም የተገልጋዩ እንግልት እና ብለሹ አሠራሮችን ለመቀነስ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ መኾናቸውን ተናግረዋል። የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መኾኑንም አስረድተዋል።
ቀጣይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የመንግሥት ሠራተኞች በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የመንግሥት ሠራተኞችን አቅም በማሻሻል በተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ ታፈረ ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ተግባራትን በተሻለ ለመፈፀም መነሳሳትን የፈጠረ መኾኑንም አንስተዋል። የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ማጣራት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ተወዳዳሪ ሲቨል ሰርቫንት ለመፍጠር የፈፃሚውን እና የአስፈፃሚውን ብቃት በማሳደግ የሚጠበቀውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግሥት ያስቀመጣቸውን የልማት እና ሌሎች ተግባራት ለማከናወን የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ሰፊ መኾኑን ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችን አቅም በማሻሻል የተቋማትን የመፈፀም አቅም ማጎልበት ይገባልም ነው ያሉት።
አሁንም ቢኾን ለተገልጋዮች ተገቢ አገልግሎት እየተሰጠ አለመኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎች ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
መንግሥት ለመንግሥት ሠራተኞች ያደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የሚበረታታ መኾኑን ያነሱት ተሳታፊዎች የሪፎርም ተግባራትን ለማሳለጥ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በመድረኩ በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ ለፈፀሙ ሠራተኞች ዕውቅና ተሰጥቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
