
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን፣ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር፣ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች በተገኙበት በሴት ተማሪዎች ትምህርት ዙሪያ ውይይት ተካሄዷል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጠረው የሰላም እጦት በሴት ሕጻናት ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጠናጋሻው ተናግረዋል።
ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት መመለስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመኾኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት እየሠሩ ካሉ ድርጅቶች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ሰብከት የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለዕድሜ ጋብቻ ማስወገድ አሥተባባሪ ጌቱ መንግሥቱ እንደተናገሩት በሕጻናት ላይ የሚደርሱ የኀይል ጥቃቶችን በመከላከል ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ከጎጥ እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አደረጃጀት በመፍጠር መብታቸው እንዲከበር እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሴት ሕጻናትን ከትምህርት ገበታ መነጠል የትውልድ ስብራት መፈጠር መኾኑን የተረዳ ማኅበረሰብ እንዲኖር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ አስተያየት የሰጡ ሕጻናት በዞኑ በግጭት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባት ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት የመመለስ ሥራ መንግሥት እና በማኅበረሰቡ ትብብር እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
በተለይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማኅበረሰቡ ለነገ ትውልድ በማሰብ ሊታገላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ “የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት’ በሚል መሪ መልዕክት እንዲሁም የልጃገረዶች ቀን “የእኔን ለውጥ የምመራ ታዳጊ ነኝ” በሚል መሪ መልዕክት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።
ዘጋቢ:- አበበች የኋላሸት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
