
ደብረ ታቦር: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን አቅም በማሳደግ እና የእንችላለን መንፈስን በማጠናከር በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መሥራት መሠረታዊ ነገር ነው።
ደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የሚገኘው ታቦር አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ እና ልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት በበጀት ዓመቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክሮ የቀጠለ ትምህርት ቤት ነው።
ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተቀብሎ በትኩረት መማር ማስተማሩን እያሳለጠም ይገኛል።
ተማሪ እናነው መብሬ እና ካሳሁን ፈረደ የልዩ ፈላጎት ትምህርት መማራቸው ትልቅ አብርክቶ እንደሰጣቸው ተናግረዋል። አሁን በጣም ደስተኞች ነን ከሰው ጋር መዋል ችለናል ይላሉ ተማሪዎቹ። አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ሰብሮ ከዚህ መድረስ በጣም ፈታኘ ነበረ ነው ያሉት።
ሰዎች ዝቀተኛ ግምት እንደሚሰጧቸው እና ተምረው የትም መድረስ እንደማይችሉ የሚያስቡ እንዳሉም አንስተዋል። ይህ ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት መኾኑንም ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት እንደገጠማቸው እና እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል።
በትምህርት ቤቱ የልዩ ፍላጎት መምህር የኾኑት ሐብታሙ ገደፋው ውስንነቶች ያሉ ቢኾንም እንኳ የመስማት፣ የማየት፣ የዐዕምሮ እድገት ውስንነት እንዲሁም የባሕሪ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎችን በመለየት ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። ችግሮችን ለመፍታት ግን ሁሉም ባለቤት መኾን ይኖርበታል ነው ያሉት።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ፀጋዬ አስማረ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ለማስተማር መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲኾኑ የድምጽ ማጉያ፣ ዊልቸር፣ መነጽር፣ እና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እየበሩ አዕምሮ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ከመደበኛው ትምህርት ጋር ሲነጻጸር የተሰጠው ትኩረት ክፍተቶች ያሉበት እንደኾነ ተናግረዋል።
በአተገባበር ደረጃ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አካቶ ከተቀላቀሉ በኋላ ውጤታማ የማይኾኑበት ምክንያት መምህራን የልዩ ፍላጎት ትምህርት አሰጣጥ ላይ የግንዛቤ ችግር ስላለባቸው ነው ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት ለመምህራን ሥልጠና መስጠትን እና ግንዛቤ መፍጠርን እንደመፍትሄ ተወስዷል ነው ያሉት።
በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እና ርብርብ በማድረግ ተማሪዎችን ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
