
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነት እና ይዞታ ከፖሊሲም በላይ በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚመራ መሠረታዊ ሀብት ነው፡፡
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የመሬት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ እንደኾነ ተደንግጓል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ኾኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ ቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ የሚያስችል ድንጋጌ በዚሁ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 8 ሥር ተቀምጧል፡፡
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና የልማት ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰንም አዋጅ ቁጥር 1161/2011 ወጥቷል።
በዚህ አዋጅ መሠረት በፌዴራል መንግሥት ለሚሠሩ መሠረተ ልማቶች ለልማት ተነሺዎች የካሳ እና መልሶ ማቋቋሚያ ክፍያ በፌዴራል መንግሥት ሲፈጸም ቆይቷል።
ይህ አዋጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 በሚል ተሻሽሏል። በፌዴራል ደረጃ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ሢሠሩም ለልማት ተነሺዎች ካሳ እና መልሶ ማቋቋሚያ ገንዘብ የሚከፍሉት የክልል መንግሥታት እንደኾኑ ደንግጓል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያም አዋጁ ከመሻሻሉ እና ከተሻሻለ በኋላ ለልማት ተነሺ ባለ ይዞታዎች በወቅቱ ካሳ ለመክፈል እና ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ከባለጉዳዮቹ በመነሳት ጠይቋል።
የባሕር ዳር – ጭስ ዓባይ የመንገድ ፕሮጀክት ተነሺ እና ካሳ ተከፋይ አርሶ አደር እንደሚሉት የእርሻ እና የአትክልት የመሬት ይዞታቸው ለመንገድ ግንባታ ተወስዷል። የካሳ ክፍያ ተገምቶላቸውም የውሳኔ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው ነግረውናል። የሰነድ ማስረጃውንም አረጋግጠናል።
የመንገድ ሥራው ሲጀመር ለልማቱ ደስተኛ ኾነው የዘሩት ሰብል ለአጨዳ ሳይደርስ መተባበራቸውንም አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ አርሶ አደሩ ይህ የካሳ ግምት ከተወሰነ ከአራት ዓመታት በላይ ቢቆጠሩም እስከ አሁን የካሳ ክፍያ አልተከፈለኝም ነው ያሉት። የግምት ካሳቸው እንዲከፈላቸው የሚመለከታቸውን የሥራ ኀላፊዎች በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ እና እየተንገላቱ እንደኾነ ነግረውናል። አሁንም የተገመተላቸው የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።
ሌላኛው የባሕር ዳር- ጭስ ዓባይ የልማት ተነሽም ካሳ ሳይከፈላቸው መቆየቱን ነግረውናል። አሁን ላይ ጉዳዩን ወደ ሕግ በመውሰድ በጠበቃ ሲከራከሩ ቆይተው ካሳ እንደተከፈላቸው ነው የጠቀሱት። ለልማት የይዞታ መሬታቸው ሲወሰድ ካሳ የማግኘት እና በወቅቱ ተከፍሏቸው ራሳቸውን የማቋቋም መብት በአዋጅ ቢደነገግም ይህ ባለመተግበሩ ላልተገባ ወጭ እና እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ ደግሞ በልማት ተነሽዎች ካሳ ምክንያት የቆሙ እና በተፈለገው ጊዜ ያልተጠናቀቁ የመስኖ፣ የመንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በክልሎች ላይ ይታይ የነበረ የልማት ተነሺዎች ካሳ ግምት እና አከፋፈል ክፍተት ይታይበት የነበረ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥት የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ እና መልሶ ማቋቋም ሥራ ወደ ክልሎች ማዛወሩን ገልጸዋል። አሁንም ግን የልማት ተነሺዎች ካሳ ተገምቶላቸው በወቅቱ ያለመክፈል ውስንነት መኖሩን አንስተዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ መሬት ቢሮ ጉዳዩን በባለቤትነት ይዞ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አብራርተዋል።
የካሳ ግምት በተሻሻለው አዋጅ መሠረት በአግባቡ እንዲፈጸም እና የልማት ተነሺዎች የሚያጋጥማቸው እንግልት እንዲፈታ፣ የልማት ተነሺዎችም የተሻለ ካሳ ለማግኘት በሚል ተገቢ ያልኾኑ ተግባራትን እንዳይፈጽሙ መክረዋል። በመንግሥት በኩልም ለልማት ተነሺዎች በተገቢው ሁኔታ እና ጊዜ የካሳ መክፈል እና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች እንዲከናወኑ ቋሚ ኮሚቴው የተጠናከረ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሰይፉ ሰይድ በክልሉ ከልማት ተነሺዎች ጋር ተያይዞ ካሳ የመክፈል እና መልሶ የማቋቋም ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። በሂደቱ የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ክፍተቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
በፌዴራል መንገዶች አሥተዳደር የካሳ ክፍያ የሚፈጸመው የባሕር ዳር ጢስ ዓባይ መንገድ ፕሮጀክት የልማት ተነሺዎች እና ሌሎች እየተሠሩ ያሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ካሳ ሳይከፈላቸው ለተነሱ ባለይዞታዎች ካሳ እንዲከፈላቸው የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
1161/2011 አዋጅ ከመሻሻሉ በፊት ለመንገድ ፕሮጀክቶች ለተነሱ 23 ሺህ 308 ባለይዞታ የልማት ተነሺዎች 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ በፌዴራል መንገዶች አሥተዳደር አለመከፈሉንም ጠቁመዋል።
በፌዴራል መንገዶች አሥተዳደር ካሳ ለሚከፈላቸው የባሕር ዳር – ጢስ ዓባይ መንገድ ፕሮጀክት የልማት ተነሺዎች እና ለሌሎችም የልማት ተነሺዎች የተገመተላቸው ካሳ በአግባቡ እንዲከፈላቸውም ከተቋሙ ጋር ውይይት እየተደረገ መኾኑን አስገንዝበዋል። ጉዳዩን የክልሉ መንግሥት በትኩረት ይዞ እየሠራ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
አዋጁ ከተሻሻለ በኋላ ደግሞ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1336/2016 መሠረት ከሐምሌ 04/2016 ዓ.ም በኋላ ያለውን በፌዴራል ተቋማት ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ካሳ የአማራ ክልል መንግሥት እየከፈለ መኾኑን ተናግረዋል። ለአብነትም የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ የመገጭ እና የአጅማ ጫጫ መስኖ ፕሮጀክትን አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት “የመጀመሪያው ሩብ ዓመትም ለ3 ሺህ 479 የልማት ተነሺ ባለይዞታዎች 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን” ተናግረዋል። በሩብ ዓመቱ ከታቀደው አንጻር አፈጻጸሙም 92 በመቶ እንደኾነ አሥረድተዋል።
በፌዴራል መንግሥት በኩል የሚከፈል የካሳ ክፍያም ሙሉ በሙሉ የቆመ አይደለም፤ እየተከፈለ ነውም ብለዋል። ፕሮጀክቶች ካላቸው ቁጥር አንጻር ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ መፈጸም አለመቻሉን ነው የተናገሩት።
ካሳ ሳይከፈላቸው ለረጅም ጊዜ የቆዩ የልማት ተነሺዎች መጉላላት እንዳይገጥማቸው እየተወሰደ ያለው መፍትሔ ምን እንደኾነ አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምክትል ቢሮ ኀላፊው የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች እንዳይጓተቱ ካሳን በወቅቱ መክፈል የተቋማቱ ግዴታ ነው ብለዋል።
በተለያየ ምክንያት ያጋጠሙ ውስንነቶችን አርሞ ለተነሺዎች በአሠራሩ መሠረት ተገቢ ካሳ መክፈል ይገባልም ነው ያሉት። ይህ እንዲኾንም አዋጁ ከተሻሻለ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ መንግሥት የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ እና መልሶ ማቋቋም ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ከስር ከስር እየተከፈሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። አፈጻጸሙም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
እስከ አሁን በክልሉ 215 ሺህ 850 ባለይዞታዎች በልማት ምክንያት ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረገ ሲኾን
የልማት ተነሺዎችን በወቅቱ መልሶ ከማቋቋም አኳያም የክልሉ መንግሥት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በጀት በመመደብ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። በ2018 በጀት ዓመትም የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ቀጣይ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የጎላ ችግር እንደማይኖርም ገልጸዋል። የመልሶ ማቋቋም ሥራ ግን ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም በትብብር ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚሠራ በመኾኑ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል። አስቻይ ሁኔታዎች ሲኖሩ ግን የልማት ተነሺዎችን መልሶ ለማቋቋምም ነባራዊ ሁኔታቸውን ታሳቢ እየተደረገ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ልማት መኖሩ ስለማይቀር የልማት ተነሺዎችን ከመነሳታቸው በፊት ተመጣጣኝ የካሳ ክፍያ የመክፈል እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በአዋጅ ቁጥር 1161/2011 ካሳ ይከፈላቸው የነበሩ እና ያልተከፈላቸው የልማት ተነሽዎች ካሳ እንዲከፈላቸውም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ችግሩን እንደሚፈታ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
