“በዓለም ላይ ካለው ነገር ሁሉ ሽታው እጅግ ደስ የሚል እና ልብ የሚመስጥ ምንድን ነው?“

5
ባሕር ዳር: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አጼ ቴዎድሮስ አንድ ቀን ከመኮንኖቻቸው ጋር ሲጫወቱ በድንገት በጨዋታው መሐል“በዓለም ላይ ካለው ነገር ሁሉ ሽታው እጅግ ደስ የሚል እና ልብ የሚመስጥ ምንድን ነው?“ ብለው ጠየቁ። መኳንንቱ ሁሉ የሚያውቁትን የሽቶ ዘር እና ሌላም ሁሉ ነገር ተናገሩ።
አጼ ቴዎድሮስም ሁሉንም አላወቃችሁትም ካሉ በኋላ “የሕጻን ልጅ ጠረን ነው“ ብለው መልሰውላቸዋል። ይህ የታሪክ ትውስታ አጼ ቴዎድሮስ ለልጅ የነበራቸውን ፍቅር የሚያሳይ እና ልዑል ዓለማየሁን ከወለዱ በኋላ ከልዑሉ ጋር እየተጫወቱ የሚያሳልፏቸው ጊዜያት እንደነበሩ እና ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡
ጳውሎስ ኞኞ “አጼ ቴዎድሮስ“ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቴዎድሮስ ስድስት ልጆች እንደነበሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከስድስቱ ልጆቻቸው መካከል ልዑል ዓለማየሁ ከትግራዩ የመጨረሻው የዘመነ መሳፍንት ባላባት የደጃች ውቤ ልጅ እቴጌ ጥሩ ወርቅ ነው የተወለደው፡፡
ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ሚያዝያ አምስት 1853 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ እንደተወለደ ታሪክ ያስረዳል። ሕጻኑ በተወለደ ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ እጅግ ተደስተው መድፍ እና ጠመንጃ ማስተኮሳቸውን፣ አምስት መቶ ያህል እስረኞችንም መፍታታቸውን ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።
ከልጃቸው ጋርም ሲጫወቱ መዋል ያስደስታቸው ነበር፤ በተበሳጩ ጊዜ ዓለማየሁን አቅፈው ሲስሙ ሁሉንም ነገር ይረሱ ነበርም ይላሉ።
አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ ከእንግሊዞች ጋር ጦርነት ገጥመው ራሳቸውን ባጠፉ ወቅት ዓለማየሁ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። ንጉሡ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ ሕጻኑ እና እናቱ እቴጌ ጥሩ ወርቅ ከእንግሊዝ ወታደሮች ጋር ወደ እንግሊዝ ጉዞ ጀምረው የነበረ ቢኾንም እቴጌዋ አንጣሎ አጠገብ ሐይቅ ሀላጥ የተባለ ስፍራ ሲደርሱ በሕመም ምክንያት ሕይዎታቸው አለፈ። ይህም ለትንሹ ልዑል ከአባቱ ህልፈት ጋር ተደምሮ ድርብ ሃዘን ፈጥሮበታል፡፡
እቴጌ ጥሩ ወርቅ ከመሞታቸው ቀደም ብሎ ለእንግሊዛዊው ካፒቴን ስፒዲ“ልጄ አባት የለውም፤ እኔም እናቱ ልሞት ነው፡፡ በሚሄድበት ሀገር ዘመድ ስለሌለው አንተ ዘመድ ሁነው፡፡ አባት ስለሌለው አንተ አባት ሁነው፡፡ ይሄን ያልኩህን እንደምታደርግለት በእግዚአብሔር ማልልኝ” እንዳሉት እና ካፒቴን ስፒዲ በኋላ ላይ በጻፈው መጽሐፍ እቴጌዋ የጠየቁትን እፈጽማለሁ ብሎ እንደማለ ጳውሎስ ኞኞ ጠቅሰዋል፡፡
ልዑል ዓለማየሁ ወደ እንግሊዝ የተወሰደው ፌሬዝ በምትባል መርከብ ሰኔ 4/1860 ዓ.ም ነበር። ካፒቴን ስፒዲ ትዳር ሳይመሠርት የቆየ ስለነበር ለዓለማየሁ ጥሩ አሳዳጊ እና እናት የምትኾን ወይዘሮ ኮታም የተሰኘች ሴትን መርጦ አገባ። ወይዘሮ ኮታም ከዓለማየሁ ጋር በፍጥነት ተወዳጀች፤ ጥሩ አሳዳጊም ኾነችው።
ኾኖም የልዑል ዓለማየሁ ቀጣዩ ዕጣ ፋንታ እንደተጠበቀው አልነበረም። ምክንያቱም ምንም እንኳ ስፒዲ ለልጁ በማሰብ ሚስት ለማጋባት ቢወስንም ሥራውን መሥራት ስለነበረበት በወቅቱ ወደ እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሕንድ የስምንት ዓመቱን ዓለማየሁን እና ሚስቱን ይዞ አቀና። በሕንድ በኖሩበት ሁለት ዓመታት ውስጥ ዓለማየሁ በትምህርቱ መጎበዝ መጀመሩ እና አልፎ አልፎ ከመታመሙ ውጭ ጥሩ ሁኔታ ላይ መኾኑን ስፒዲ በመጀመሪያ ጹሑፉ ጠቅሶ ነበር፡፡
ይሁንና የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናት “ህንድ ለልዑል ዓለማየሁ ትምህርት ተመራጭ አይደለችም፤ ወደ እንግሊዝ ይመለስ እና ጥሩ ትምህርት ይከታተል” የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ሕጻኑ ከሲፒዲ ጥገኝነት መውጣት እንዳለበት እና ራሱን መቻል እንደሚያስፈልገውም ጠቀሱ። ሃሳቡ ከፍተኛ ክርክር አስነሳ::
ስፒዲ እና ሚስቱ ዓለማየሁን በሕንድ አሳልፎ ላለመስጠት እጅግ ቢሟገቱም የእንግሊዝ መንግሥት ልዑሉ ከሕንድ እንዲመለስ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ዓለማየሁ በስፒዲ አንገት ተጠምጥሞ “አባቴ አንተ ነህ፣ ያለ አንተ መኖር አልችልም። እባክህ ከአንተ አትለየኝ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ አብሬህ ልሂድ፤ ያለዚያ እሞትብሀለሁ“ብሎ መናገሩን ጳውሎስ ኞኞ ጽፈዋል።
ልዑል ዓለማየሁ ቄስ ብላንኬ ለሚባል ዘጠኝ ሴት ልጆች ላሉት ሰው ተሰጠ። በቤቱ ውስጥ ብዙ ልጆች ስላሉ ልዑል ዓለማየሁ ባይተዋር እና ብቸኛ እንዳይኾን ታስቦ ነበር ውሳኔው የተላለፈው። የካፒቴን ስፒዲ ጥገኛ እንዳይኾን እና በትካዜ ተውጦ ጊዜውን እንዳያሳልፍ በሚልም በሳምንት 31 ሰዓት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ተደርጎ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ቤት ውስጥም እንደታሰበው ከባይተዋርነት እና ናፍቆት ሊወጣ አልቻለም። ሰውነቱ ገርጥቶ መጎሳቆል ጀመረ። በኋላ ላይ የልጁ መክሳት እና መጎሳቆል ንግሥት ቪክቶሪያን ጭምር ያስደነገጠ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ከአያቱ (ከጥሩ ወርቅ እናት) የተጻፈ ደብዳቤ ወደ እንግሊዝ ይደርሳል። ደብዳቤው የተጻፈው በአማርኛ በመኾኑ ተርጉሞ የሚያቀርበው ሰው አስፈለገ። በዚህም የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዎልድሜር የተባለውን ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ አጼ ቴዎድሮስ የሚወዱት እና የሚያከብሩት መልዕክተኛን ፈልጎ አገኘ።
ዎልድሜር ደብዳቤውን ተርጉሞ በእንግሊዝኛ አቀረበ። የደብዳቤውም ይዘት ልዑሉ ለምን ለአያቱ ደብዳቤ እንደማይጽፍ፣ ወደ ሃበሻ ምድር ከቤተሰቦቹ እና ከወገኖቹ ጋር መቀላቀል እንዳለበት እንዲሁም የሀበሻ ሕዝብም የልዑሉን ተመልሶ መምጣት በጉጉት እንደሚጠብቅ የሚጠቅስ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ስለደብዳቤው እና ስለተሰጠው ምላሽ የሚታወቅ ነገር እንደሌላ ጸሐፊያን ጠቅሰዋል።
ልዑል ዓለማየሁ በቄስ ጄክስ ብላክ ቤት እንዳልተመቸው ከታወቀ በኋላ በተለያዩ እንግሊዛዊያን ሰዎች ቤት እንዲኖር ተደርጓል። ኾኖም ከሁሉም ጋር በነበረው ቆይታም ስላልተመቸው በመጨረሻ ስሪል ራምሶን ከተባለ ሰው ጋር እንዲቆይ ተደረገ። ራምሶን ለዓለማየሁ የተመቸ ነበር። ከራምሶን ጋር የቆየው ዓለማየሁ የራግቢ እና የእግር ኳስ ጨዋታ ዝንባሌ እንደነበረው እና የትምህርት አቀባበሉም እጅግ ጥሩ እንደነበር ይነገራል።
በዚያው እንደቆየ በጥቅምት ወር ታመመ። ኖርዝ ኮት የተባለ ሐኪም ስለ ዓለማየሁ ሕመም ለሚመለከታቸው በጻፈው ደብዳቤ “አደገኛ ሕመም መታመሙን እንድታውቁ ይሁን። ምንም ጥረት ብናደርግ ሕመሙ እየጸናበት ሔደ ሕመሙ አደገኛ በመኾኑ እና በጣም ስለጠናበት አሁን ምግብ አይበላም፤ መድኃኒትም አይወስድም”ሲል ገልጿል።
ንግሥት ቪክቶሪያን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት መታመሙን ሲሰሙ ተጨነቁ። ንግሥቷም ማጽናኛ ደብዳቤ ላኩለት። ልዑሉ ከንግሥቲቷ ደብዳቤ እንደመጣለት ሲያውቅ ተደሰተ። ነገር ግን ከሕመሙ የተነሳ አንብቦ ሊጨርሰው አልቻለም። በቅርብ ደብዳቤውን ከሚያይበት ቦታ እንዲቀመጥለት ጠይቆ ተቀመጠለት። ብዙም ሳይቆይ በዚህ ሳምንት ሕዳር 5/1872 ዓ.ም በተወለደ በ19 ዓመቱ ሕይዎቱ አለፈ። በንግሥቷ ትዕዛዝም ዊንድሰር በሚገኘው የነገሥታት መቀበሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጸመ።
👉የዩኔስኮ ምሥረታ
የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በኋላ በዚህ ሳምንት ኅዳር 07/1938 ዓ.ም በእንግሊዝ ለንደን ተመሠረተ።
ድርጅቱ በ1945 ነው የተቋቋመው። የጦርነቱ ተፋላሚዎች የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩ እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ ስምምነቶችን መፈራረማቸው በቂ አይደለም ብሎ የተነሳው ዩኔስኮ መላው ዓለምን በሚያስተሳስሩ እና የጋራ መግባባት በሚፈጥሩ ቅርሶች ላይ ሢሠራ ቆይቷል።
በፈረንጆቹ 1972 ዓ.ም የዓለም ቅርስ ኮንቬንሽንን አውጥቶ የሰው ልጅ ድንቅ የጥበብ ውጤት የኾኑ ድንበር ተሻጋሪ ሰው ሠራሽ ወይም ባሕላዊ ቅርሶች እና የተፈጥሮ ሃብቶችን በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ጀምሯል። ዩኔስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ቅርስ አድርጎ የመዘገበው በኢኳዶር የሚገኙትን የጋላፓኮስ ደሴቶች እና ውብ መልከዓ ምድርን ነበር።
ድርጅቱ እስካሁንም በ168 ሀገራት የሚገኙ ከ1ሺህ 199 ቅርሶች በላይ የዓለም ቅርስ አድርጎ መዝግቧል። ጣሊያን፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በርካታ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ናቸው።
ኢትዮጵያም ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በማስመዝገብ 30ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ምንጭ፦ የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ድረ ገጽ ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleተሠርተው የሚፈርሱ ሳይኾን በጠንካራ ፕላን እየተመሩ የሚዘልቁ ከተሞች መፍጠር ይገባል።
Next articleበኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል የአማራ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ምሥረታ እየተካሄደ ነው።