
አዲስ አበባ: ኅዳር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በከተማ አመሠራረት ታሪክ ቀዳሚ ከኾኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከተሞች በኢትዮጵያ ነበሩ።
በታላቅነት ተመሥርተው የነበሩ፣ በመናገሻነት ያገለገሉ፣ አሁን ግን ከነበሩበት ከፍታ ዝቅ ብለለው የምናገኛቸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ከተሞች አሉ። ብቻ ከተሞች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይጠፋሉ።
በኢትዮጵያ ለከተሜነት መመሥረት በርከት ያሉ መነሻዎች ይጠቀሳሉ። የነገሥታት መናገሻዎች ለከተሜነት መመሥረት ምክንያት ኾነዋል። በኢትዮጵያ የተመሠረቱ በርካታ ከተሞች ከዚሁ ጋር ይገናኛሉ። የወታደራዊ ካምፖች ወደ ከተማነት አድገዋል። መገበያያ የነበሩ አካባቢዎችም ለከተማ መመሥረት መሠረት ከኾኑት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ18ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የከተሜነት ምሥረታ ፈጣን አንደነበር የከተማ ልማት ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ.ር) ተናግረዋል። የዩኤን ሀቢታት ጥናት እንደሚያመላክተን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2007 ላይ የከተማ ነዋሪዎች የገጠር ነዋሪዎችን የበለጡበት ዓመት እንደነበር ያትታል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም በዓለም የመረጃ ቋት ውስጥ ይህንን አካትቷል ይላሉ ባለሙያው። አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊዮን ሰዎች በከተሞች ይኖራሉ። ይህ አሃዝ ባደጉ ሀገራት እና በማደግ ላይ ባሉ መካከል ልዩነት ይታይበታል ብለዋል ባለሙያው።
በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የከተሜነት እድገት እጅግ ፈጣን ነው። ለአብነት የኢትዮጵያን ብንመለከት በየዓመቱ የ5 ነጥብ 4 በመቶ የከተሜነት እድገት እንዳለ ከከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል። በየ ዓመቱ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ሕዝብ ቁጥሩ ከፍ ያለ እንደኾነም መረጃዎች ያሳያሉ ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ፈጣን የከተማ እድገት ከሚታይባቸው ሀገራት አንዷ ናት። የከተማ ልማት ባለሙያው አበበ ዘልዑል በኢትዮጵያ የክትመት ምጣኔ ዝቅተኛ መኾን ተስፋም ስጋትም ነው ይላሉ። የከተማ ምጣኔ ዝቅተኛ መኾን በዕቅድ ተመርተን ከተሞችን በአግባቡ ማልማት ከቻልን የተሻለ ከተማ ለመመሥረት ያስችላል ነው ያሉት።
በግዴለሽነት ከኾነ እና ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን የተበላሸ ከተማ መመሥረቱ አይቀርም ባይ ናቸው። ይህ ማለት በፕላን ያልተደራጀ ከተማ ይመሠረታል፤ መሠረተ ልማት በአግባቡ ያልተሟላለት ከተማ እንዲኖር ያደርጋል ነው ያሉት። ከተሞችም ለነዋሪዎች ምቹ እንዳይኾኑ ያደርጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ አዳዲስ ከተሞች በብዛት እየተመሠረቱ ያሉት የመንገድ ዝርጋታን ተከትሎ ነው። ነገር ግን ከዚህ የተለየ አተያይ መኖር እንዳለበት የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይመክራሉ። ከተሞችን አቅዶ መገንባት ይገባል። ቦታ መርጦ እና ሀብታቸውን አጥንቶ እና መሠረተ ልማት አሟልቶ ሰዎች ወደ ከተማ እንዲገቡ ማስቻል ይገባል ይላላሉ።
“አዳዲስ ከተሞች ሲገነቡ ነገ እንደማይፈርሱ እርግጠኛ መኾን ይገባል” የሚሉት የከተማ ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች ይህን ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ የከተሜነት ካርታ ሥርዓትን ማዳበር እና ከተሞችን በአግባቡ በፕላን መምራት ይገባል ነው ያሉት።
ፕላናቸው ለረዥም ዘመናት የሚዘልቅ፤ ለመልሶ ግንባታ ድጋሚ ወጭ የማያስወጣ፤ ለምጣኔ ሃብት መሠረት የሚኾን፤ የተቀላጠፈ የተሽከርካሪ ፍስሰት እንዲኖር የሚያግዝ፤ አካባቢን ከብክለት ነጻ የሚያደርግ፤ መዝናኛ እና የቱሪስት መዳረሻ የሚኾን ከተማ መገንባት ያስፈልጋል ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በአፋር ክልል በመካሄድ ላይ የሚገኘውን 10ኛው የከተሞች ፎረም ተከትሎ በኢትዮጵያ የከተማ አመሠራረት፣ እድገት እና ወደፊት የኢትዮጵያ ከተሞች መምሰል በሚገባቸው መልክ ዙሪያ የፓናል ውይይት አድርጓል።
ዘጋቢ:- ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
