
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፖሊስ የተሰጠውን ሙያዊ ኀላፊነት በመወጣት ፍትሕ ፈላጊውን ሕዝብ መታደግ እና ለበለጠ ግዳጅ መዘጋጀት ይገባዋል ሲል የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
ዞኑ በሕግ ማስከበር ተልዕኮ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመደበኛ እና አድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የዕውቅና እና የማዕረግ ዕድገት ሰጥቷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው ግጭት ክልሉ እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሰው እና ንብረት መጥፋት ባሻገር ለፖለቲካዊ፣ ለማኅበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎት ቆይቷል።
የፖሊስ መሪው እና አባላት ሰላምን ለማስፈን ዋጋ ከፍለዋል ያሉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ግርማ ጫኔ አሁን ላለው አንጻራዊ ሰላም መስፈን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበዋል።
በዕውቀቱ የዳበረ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ብቁ የኾነ ፖሊስ ሕዝብ እና መንግሥትን ማገልገል አለበት ነው ያሉት። በሰብዓዊነት እና በጀግንነት ሀገርን ብሎም ሕዝብን ማገልገል ከፖሊስ ይጠበቃልም ብለዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሐኑ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማስፋት እና ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በአካባቢው የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሐኑ ጥላሁን ዕውቅና እና ሽልማት የበለጠ የሚያበረታታ በመኾኑ ከሕዝብ ጋር ግዳጅ እና ተልዕኮን ልትወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ ግዳጆች የተሳተፉ እና ውጤት ያስመዘገቡ የመደበኛ እና አድማ መከላከል የፖሊስ አባላት የተደረገላቸው ሽልማት እና ዕውቅና እንደሚያበረታታቸው እና የሕዝብን ሰላም ለመመለስ እንደሚተጉ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
