
ባሕር ዳር: ኅዳር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና” ስምን መልአክ ያወጣዋል” እንዲሉ የቀጣናው ቀንደኛ ተዋንያኖች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ የተዋንያኑ መበራከት ብቻ ሳይኾን ፍላጎቶቻቸውም ጉራማይሌ የሚባል ዓይነት ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲን ያካካተተው የአሕጉሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል የዓለም ኃያላን ሀገራት ዐይን እና ትኩረት ያረፈበት ክፍል ነው፡፡ ይህም ቀጣናውን “ለውስጦቹ ቀጋ፤ ለውጮቹ አልጋ” አድርጎት ቆይቷል፡፡
የቀንዱ ጂኦ ፖለቲካል ተጽዕኖ ከቀጣናው ሀገራት ባለፈ የዓለምን ሰላም፣ ንግድ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የመበየን አቅም እንዳለውም ይነገራል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት የጀመረው ቀድም ባሉት ጊዜያት ቢኾንም ለአካባቢው ሀገራት እና ሕዝቦች ትኩሳት እስኪኾን ድረስ በውጭ ኃይሎች መዳፍ ስር የወደቀው ግን በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1889 የስዊዝ ካናል ከተከፈተ በኋላ እንደኾነ ይነገራል፡፡
በቀንዱ ውስጥ ብዙ ሀገራት ቢኖሩም በልዩ ልዩ ገዥ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሚና ታሪካዊ፣ ዕድሜ ጠገብ እና ተፅዕኖው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ሀገሪቷ የአፍሪካ አሕጉር የውኃ ማማ መኾኗ በጎረቤቶቿ ዘንድ ተጽዕኖዋ እስከ ሕልውና የሚድርስ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያ 100 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በየዓመቱ ለጎረቤቶቿ በነጻ እንደምትሰጥም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እንዳለመታደል ኾኖ ግን በየዓመቱ ውኃ በነጻ የምትለግሳቸው ጎረቤቶቿ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ምቾት ከመፍጠር ይልቅ ሳንካ ኾነውባት ቆይተዋል፡፡ በተለይም የግብጽ እና ሱዳን ዘመን ጠገብ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓባይ ወንዝ ውኃ ላይ የተመሠረተ ኾኖ ቆይቷል፡፡
ከ85 በመቶ በላይ በዓባይ ወንዝ ውኃ ላይ አበርክቶ እና ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግሉል ኾና የመቆየቷ ምስጢርም ከዚህ ሴራ የሚመዘዝ ኢ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንደነበር የዓደባባይ ሀቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የድኅረ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ፖሊሲ ቅኝት ግን የቅኝ ግዛት ዘመንን የውኃ ትርክትን ሽሮ አዲስ የጂኦ ፖለቲካል ስትራቴጂክ ለውጥ የፈጠረ እንደኾነ መታየት ጀምሯል፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ በአሕጉሪቷ ግዙፍ የተባለለትን ግድብ ገንብታ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ትኩረቷን እና ፍላጎቷን ወደ ሌላኛው ተፈጥሯዊ የውኃ ክፍሏ አዙራለች፡፡
አክሊሉ ከበደ “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ከጥንት እስከ ዛሬ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጻሕፋቸው ኢትዮጵያ በአካባቢው ላይ ግዙፍ ሀገር እንደመኾኗ፣ ሕዝቧም ኾነ ኢኮኖሚዋ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ በመኾኑ ያለ ባሕር በር የምትቀጥልበት ሁኔታ አስቸጋሪ ይኾናል ይላሉ፡፡
የባሕር በር ለሥልጣኔ ያለው ወሳኝነት በየትኛውም ሀገር ታሪክ ውስጥ የታየ ሀቅ ነው፡፡ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያም በአክሱም ሥልጣኔ ተጠቃሽ ስትኾን በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ገናና የንግድ እንቅስቃሴ ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡
እውቁ ዲፕሎማት እና ጸሐፊ አክሊሉ ከበደ እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የመነሳት እና የመውደቅ ተረኮች ከባሕር በር ጋር በነበራት ቅርበት እና መራቅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ታይቷል፡፡ የባሕር በር በነበራት ዘመን ገናና ሥልጣኔን ለዓለም ያስተዋወቀች ኢትዮጵያ ከባሕር በር ስትርቅ ደግሞ ምን ያህል የተጽዕኖ ደረጃ እንደሚጫናት ከዚህ ጊዜ የተሻለ የታሪክ ማጣቀሻ ማቅረብ አያስፈልግም ባይ ናቸው፡፡
ለኢትዮጵያ የባሕር በር የሕልውና ጉዳይ ነው የሚሉት የአማራ ክልል የሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ጥያቄው የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይኾን የመጻዒውን ትውልድ እጣ ፋንታም የመበየን አቅም እንዳለው ያነሳሉ፡፡
የባሕር በር የመጻኢዋን ኢትዮጵያ መዳረሻ የሚወስን በመኾኑ በቸልታ ሊታይ እንደማይገባው ጠቅሰዋል። ምሁራን፣ ተቋማት፣ የፖለቲካ ልሂቃን እና ወጣቶች በትኩረት መከታተል እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሕግ ምሁሩ የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ የሚኾንባቸውን ሁለት ዓበይት ነጥቦችም ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ግዙፍ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ያላት እና ወደፊትም የማደግ ተስፋ ያላት ሀገር በመኾኗ ይህንን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የሚሸከም የገቢ እና ወጭ ንግድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባታል የሚል እሳቤ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚኾነው የንግድ እንቅስቃሴ በባሕር ላይ የሚካሄድ ነው፡፡ 10 በመቶው የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ደግሞ በቀይ ባሕር መስመር ይካሄዳል፡፡ እናም ኢትዮጵያ በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና እንድትጫዎት የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሕልውና ጉዳይ የሚኾንበት ምክንያት ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር ይያያዛል፡፡ ኢትዮጵያ ባልተረጋጋው እና ፍፁም ተረጋግቶ በማያውቀው የቀንዱ አካባቢ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የምትችል ሀገር ናት፡፡
ይህንንም በተደጋጋሚ ጊዜ ባሰማራችው የሰላም አስከባሪ ኃይል ብቃት አስመስክራለች። እናም የሀገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የባሕር በር ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ፣ የውኃ ፖለቲካውን በበላይነት ለመምራት እና የቀንዱን ሰላም ለማረጋገጥ ዲፕሎማሲ ቁልፍ መሳሪያ እንደኾነ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከበርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ መጠናቀቁ አሕጉራዊ የዲፕሎማሲ ድል ነው ያሉን የአውሮፓ ኅብረት እና የምዕራብ ሀገራት የኢትዮጵያ ፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ አሕጉራዊ ድርጅቶች መቀመጫ፣ መሥራች እና ንቁ ታሳታፊ ሀገር መኾኗን ያወሱት አምባሳደር ዲና ይህንን የቆየ ልምዷን፣ ተሰሚነቷን፣ ዐቅሟን እና ታሪኳን ተጠቅማ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ዜጎች ከሀገር በላይ ምንም ነገር እንደሌለ በማመን እና ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጥበብ በጋራ መቆም እና በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርባቸው አንስተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕድሎች ከዘመናት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኙ በመኾናቸው ምሁራን፣ ልሂቃን እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ልዩነት የሚፈጥሩ ሥራዎችን መሥራት እንደሚኖርባቸውም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
