
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) ገቢያቸው በፍጥነት እያደገ መምጣቱን በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በገጠር እና ከተማ አካባቢ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያገለግል ግን ደግሞ ገና ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፤ የዶሮ እርባታ፡፡ መሳሪያው ካለ እንቁላሉን እያስፈለፈሉ የአንድ ቀን ጫጩት ማከፋፈል፣ ጫጩት ማሳደግና ማከፋፈል፣ አልያም የስጋ እና የእንቁላል ዶሮዎችን አሳድጎ ምርቱን ለመሸጥ አማራጮች አሉት፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ የአየር ጸባዩ ለዚህ ሥራ ተስማሚ መሆኑ ለሥራ የተፈጠሩ ወርቃማ እጆች ታክለውበት በዘርፉ ተጠቃሚ የሆኑ እንዳሉ በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡ በአሳግርት ወረዳ ጊን ሀገር ከተማ 13 ወጣቶች በዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርተዋል፤ ሌሎች 32 ሴቶች ደግሞ በገጠሩ አካባቢ የአንድ ቀን ጫጩቶችን በመረከብና በማሳደግ ወደ ገበያ እያቀረቡ ነው፡፡
ሳምራዊት እና ጓደኞቹ በሚል ስም የተደራጁት ወጣቶች የአንድ ቀን ጫጩቶችን ተረክበውና አሳድገው 45 ቀን ሲሞላቸው ያከፋፍላሉ፡፡ ወረዳ አስተዳደሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ምቹ የእርባታ ቦታ ገንብቶ እንደሰጣቸው ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡ 225 ሺህ ብር መነሻ ካፒታልም የወረዳው ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት በብድር አመቻችቶላቸዋል፡፡ የወጣቶቹ የሥራ ፍላጎት፣ ጥንካሬ እና ተግባቦት ውጤታማ እያደረጋቸ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ “ገቢያችን በፍጥነት እና ባልጠበቅነው ሁኔታ እያደገ መጥቷል፤ ጠንክረን ከሠራን ብድራችንን በአጭር ጊዜ እንመልሳለን፤ የእኛን ብድርም ሌሎች ወስድው እንዲጠቀሙ ተደራሽ እናደርጋለን” ብለዋል ወጣቶቹ፡፡ አሁን ላይ ከ950 በላይ ጫጩቶችን እየተንከባከቡ ነው፡፡ ማስፈልፈያው ስለሌላቸው (ኢትዮ ቺክን) ከተባለ ድርጅት የአንድ ቀን ጫጩቶችን ይረከባሉ፤ ወደፊት የራሳቸው ማስፈልፈያ እንዲኖራቸው ርዕይ ሰንቀዋል፡፡
ሥራው ከፍተኛ ክትትልና እንክብካቤ እንደሚፈልግ የተናገሩት ወጣቶቹ ከወጪ ቀሪ እያንዳንዳችን በየወሩ 10 ሺህ ብር እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ ጫጩቶቹን አሳድገው 45 ቀናት እድሜ ሲኖራቸው በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች ለአርሶ አደሮች ከማከፋፈል ባለፈ ወደ ደብረ ብርሃን እና አዲስ አበባ ወስደው እንደሚሸጡም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዙር እየተንከባከቧቸው ያሉት ጫጩቶች ከ180 ሺህ ብር በላይ ዋጋ እንደሚያወጡላቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ወጣቶቹ ዘርፉን በማስፋት እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን የማርባት እቅድም አላቸው፡፡ ከወረዳው የእንሰሳት ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት እና ሌሎችም መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ እና ክትትል እንዳልተለያቸው አስረድተውናል፡፡ ዘርፉ አዋጪ በመሆኑ በወረዳው ገጠር ቀበሌ ደግሞ 32 ሴት አርሦ አደሮችም ተደራጅተው 1 ሺህ 500 ጫጩቶችን በማርባት ላይ ናቸው፡፡ አርሶ አደሮቹ ራስ አገዝ አፍሪካ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት መነሻ ካፒታል እና ስልጠና እንደተሠጣቸው አስረድተዋል፡፡ ከግብርና ሥራቸው ጎን ለጎን ዶሮ ማርባቱ ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ ብርቄ ኃይሌ በወረዳው በከተማ 13 ወጣቶች እና በገጠር 32 ሴቶች በዘርፉ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው ኑሮአቸውን እየመሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዘርፉ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በቂ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ መነሻ ካፒታል እና ምቹ የሥራ ቦታ ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ነፃ የምክር አግልግሎት፣ ለጫጩቶቹ ክትባት አንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በመማር በቀጣይ በገጠር እና ከተማ በርካታ ወጣቶችን በዘርፉ ለማሰማራት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነም ቡድን መሪዋ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው