
ባሕር ዳር: ኅዳር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተከዜ ግድብ 160 ኪሎ ሜትር ስኩየር ስፋት አለው፡፡ ግድቡ በርካታ ጥቅሞች ያሉት ነው። ከሚሰጣቸው በርካታ ጥቅሞች መካከል አንደኛው የዓሣ ሃብት ነው።
ጻዲቅ ንጋቴ የተከዜ ዓሣ ሃብት ልማት የሰላም ማኅበራት ዩኒየን ሂሳብ ሹም ናቸው፡፡ ማኅበሩ ከ160 በላይ አባላት አሉት። ከተመሠረተ ከአራት ዓመታት በላይ ኾኖታል፡፡
ይህ ማኅበር ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ዓሣን አስግሮ በመሸጥ ውጤታማ እና ተጠቃሚ እንደነበር ነው የገለጹት።
አብዛኞቹ የማኅበሩ አባላትም የራሳቸው የኾነ ጥሪት ማፍራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በደረሰው የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እና በጸጥታው ምክንያት ከፍተኛ የኾነ የዓሣ ምርት ወደ ገበያ ለማድረስ አስቸጋሪ በመኾኑ እና የገበያ ትስስር ባለመኖሩ በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ መኾኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት አንድ ኪሎ ዓሣ ከ120 ብር ባልበለጠ ዋጋ እንደሚሸጡ አስረድተዋል፡፡ በዚህም በሚፈለገው ልክ የድካማቸውን ዋጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ያስረዱት፡፡
በቀጣይ ግብዓቶች ቢሟሉ እና የገበያ ትስስር ቢፈጠርላቸው በልፋታቸው ልክ ውጤታማ መኾን እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ሲሳይ ዳኛው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚታወቅባቸው ጸጋዎች መካከል በተከዜ ግድብ የሚመረተው የዓሣ ሃብት አንዱ ነው ብለዋል።
ግድቡ በ2001 ዓ.ም ሢመሠረት በዓመት ከ10ሺህ ቶን በላይ ዓሣ ማምረት እንዲያስችል ኾኖ መገንባቱን አስታውሰዋል። ከ5ሺህ በላይ ወጣቶች በዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የማሳተፍ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ካለበት ከፍተኛ የሥርዓተ ምግብ ችግር በማላቀቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚሰጠው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
በርካታ የአካባቢው ወጣቶችን በተደጋጋሚ ሥልጠና በመስጠት፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር እራሳቸውን ከመቻል አልፎ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ እና ጥሪት እንዲያፈሩ አስችሏቸዋል ነው ያሉት።
ይህ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥርዓተ ምግብ ተጠቃሚነትን ከፍ በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ሲጫወት የቆየው የተከዜ ዓሣ ሃብት ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በርካታ የማስገሪያ ግብዓቶቹ ወድመዋል፤ ከ3ሺህ 500 በላይ የሚኾኑ በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶችም ተበትነዋል ብለዋል።
በተለይ ለገበያ ትስስሩ የሚያግዙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ችግር መኖር፣ ዓሣን ሳይበላሽ ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ተሸከርካሪዎች፣ በርካታ የሞተር ጀልባዎች መዘረፍ እና የዓሣ ማቆያ ሸዶች መውደም በሐይቁ ያለውን እምቅ የዓሣ ሃብት በማውጣት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳይኾን አድርጓል ነው ያሉት።
ከጸጥታው ችግር ጋር ተያይዞ የሕገ ወጥ ዓሣ አስጋሪዎች ዓሣዎችን ለሕገ ወጥ ገበያ ማቅረባቸውም ሌላው ችግር መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ይህ ደግሞ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ አስጋሪዎች ምርቱን ይዘው ባመረቱት ልክ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በጊዜያዊም ቢኾን ይህንን ችግር ለመፍታት እና የዓሣ ምርቱን ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ ወጣቶችን መልሶ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ሕገ ወጥ ዓሣ አስጋሪዎችን ለመከላከል ግብረ ኀይል በማደራጀት ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ሴቶች የዓሣ ማስገሪያ መረብ የሚሠሩበትን መንገድ በመፍጠር በሀገር ውስጥ የዓሣ ማስገሪያን እንዲጠቀሙ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ዓሣ አቅራቢዎችን እና ነጋዴዎችን በማቀራረብ የገበያ ትስስር ላይ መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ያለውን የዓሣ ሃብት ጸጋ በመጠቀም አካባቢውን ለመጥቀም እንዲችል ግብዓቶች እና መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ረዘም ላለ ጊዜ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ነጋ ይስማው የአማራ ክልል ለዓሣ ተፈጥሮ ወሳኙ የኾነው ውኃ በከርሰ ምድርም ኾነ በገጸ ምድር እምቅ አቅም አለው ብለዋል።
ይህንን እምቅ ሃብት በመጠቀም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ዓሣ በስፋት እየተመረተ መኾኑንም ገልጸዋል። 73 የሚኾኑ የዓሣ ማምረቻ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ግድቦች ተገንብተዋልም ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል 31 ግድቦች የዓሣ ጫጩት ተጨምሮባቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ በምርቱ ተጠቃሚ እንዲኾን እና እምቅ ሃብቱ እንዳይሳሳ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በተከዜ ግድብ ማኅበር በማቋቋም የዓሣ ማስገር ልማድ ያላቸውን እና ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል። ይህንን ሥራ ውጤታማ ለማድረግም ሥልጠናዎችን በመስጠት እና ግብዓቶች እንዲሟላላቸው ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በዓሣ ሃብት ተጠቃሚ እንዲኾኑ፣ የአካባቢው ሥርዓተ ምግብም እንዲረጋገጥ እና የኢኮኖሚያዊ አቅማቸውንም ለማሳደግ መሠራቱን ገልጸዋል።
የተከዜ ግድብ ከ95 በላይ ያለው የውኃ አካል በአማራ ክልል ላይ ባሉ መሬቶች ላይ ያረፈ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ይህንን ተከትሎ በሐይቁ ዙሪያ የሚጠቀሙ እና የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር በርካታ ናቸው ብለዋል።
ግድቡ በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ ዓሣ የሚመረትበት መኾኑንም ገልጸዋል። የዓሣ ዝርያውም በስጋ አያያዝ እና ተሎ በመድረስ የተለየ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው የዓሣ ማጓጓዣ መኪኖች፣ ለዓሣ ምርት መሠብሠቢያ የሚያገለግሉ በርከት ያሉ ጀልባዎች፣ ዓሣን ለመያዝ የሚያስችሉ መረቦች፣ ለዓሣ ማቆያ የሚያገለግሉ ዲፕ ፊሪጆች፣ ሸዶች እና በሸዶች ውስጥ የነበሩ ለዓሣ ምርቱ አገልግሎት የሚሰጡ ሙሉ ግብዓቶች የተሟላበት ተቋም ነበርም ብለዋል፡፡
ይህ ተቋም ከዓመታት በፊት በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የነበረው ንብረት ከፊሉ ተዘርፏል፤ ከፊሉ ደግሞ ተቃጥሎ ከአገልግሎት ውጭ ኾኗል ነው ያሉት፡፡
ይህንን ተቋም ቶሎ ወደ ነበረበት ለመመለስ የጸጥታው ሁኔታ አሁንም ፈተና መኾኑን ነው የተናገሩት።
ድጋፍ በማድረግ እና ግብዓቶችን በማሟላት ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ሥራውን ለማስቀጠል በርካታ ፈተናዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ወደ ነበረበት መልሶ ለማቋቋም ጥናት በማጥናት ለሚመለከተው አካል ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ የመልሶ ማቋቋም ጥያቄ በማቅረብ የሚፈታ ጉዳይ ብቻ ባለመኾኑ ቢሮው ሊመልሳቸው የሚችላቸውን አቅም በመለየት የተለያዩ ግብዓቶችን እና ቴክኒዎሎጅዎችን እንደገዛ አመላክተዋል።
በቀጣይ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ግብዓቶችን ተደራሽ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል። ሌሎች ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
