
ባሕር ዳር: ኅዳር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፌደራል ደረጃ ሞዴል ተብለው ከተመረጡት አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል አንዱ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው።
በፓርኩ ውስጥ ካሉ ኢንዱስትሪዎች መካከል የሪች ላንድ ኢንዱስትሪ ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡ ፋብሪካው በ2016 ዓ.ም ወደ ማምረት ሥራ ገብቷል፡፡
የሪች ላንድ ኢንዱስትሪያል ፋብሪካ የምርት ክፍል ኀላፊ ግርማ ሞላ ፋብሪካው ዘይት፣ የኬክ ፓውደር እና የእንስሳት መኖ እንደሚያመርት ተናግረዋል፡፡
ከምርቶቹ ውስጥ የአኩሪ አተርን በማቀነባበር የኬክ ፓውደር ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብም ነው የተናገሩት፡፡
ከሁለት ዓመት ጀምሮ ፋብሪካው ሥራ ማቆሙን የተናገሩት ኀላፊው ሥራ ካቆመበት ምክንያቶች አንዱ ፋብሪካውን በሙሉ አቅሙ ማንቀሳቀስ የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት አለመኖር መኾኑን በዋናነት ተናግረዋል፡፡
አሁን ያለው የኀይል አቅርቦት ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ አይደለም ግማሽ አቅሙን እንኳን ማንቀሳቀስ አያስችልም ነው ያሉት፡፡
ይህንን ጥያቄ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል አቅርበው “በቅርቡ የተቋረጠው የሳብስቴሽን ግንባታ ይጀመራል” ከሚል ምላሽ ውጭ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
ሌላው በቡሬ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የማሪክ ኢንዱስትሪ ነው፡፡
ማሪክ ኢንዱስትሪያል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ2016 ዓ.ም ማሽን በመትከል በአካባቢው ያሉ የበቆሎ ግብአቶችን በማቀነባበር እስታርች እና የስታርች ውጤቶችን በዋናነት የሚያመርት ነው። ዱቄት፣ የእንስሳት መኖ እና የቅንጨ ምርት በማምረትም ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሚያቀርብ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አስቻለው አዳነ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው በአፍሪካ ከሚገኙ ጥቂት ፋብሪካዎች አንዱ መኾኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ፋብሪካው በቀን እስከ 240 ቶን የማምረት አቅም አለው ብለዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ 40 ለሚኾኑ ዜጎች የቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል የፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ከሐምሌ 20/2017 ጀምሮ በሙሉ አቅሙ እየሠራ አለመኾኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የብድር አቅርቦት አለመኖር እና ሌሎች ተግዳሮቶች እንዳሉበት ገልጸዋል። የመብራት ኀይል ማነስ ትልቅ ችግር እንደኾነባቸውም ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው 24 ሰዓት የመሥራት አቅም ያለው ነው። አሁን ባለው የኤሌክትሪክ አቅም ግን 4 ሰዓት የሞላ ጊዜ መሥራት እንደማይችሉ ነው የተናገሩት፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ችግሮች ቢፈቱ ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ በቆሎን በማቀነባበር፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው አስረስ ፓርኩ ለክልሉ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ትልቅ ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለመፍጠር የሚጫወተው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል። ፓርኩ የምግብ እና ምግብነክ ማቀነባበሪያ ዘርፉን በማበረታት እና በማሳደግ አይተኬ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በአንድ ፋብሪካ ከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ትላልቅ ፋብሪካዎች የሚደራጁበት ፓርክ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት እና በሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ላይ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በቡሬ እና በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን የግብርና ምርቶች ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ እና እሴት በመጨመር በተሻለ ዋጋ በመግዛት በፓትኩ ተጠቃሚ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ 38 አምራች የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች መግባታቸውን አንስተዋል። ባለሀብቶቹ 15 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፕታል ያስመዘገቡ መኾናቸውም ገልጸዋል።
ከ38ቱ ውስጥ 23 የሚኾኑት በተለያዩ የግንባታ እና የማሽን ተከላ ሂደት ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ በቅድመ ግንባታ ደረጃ ላይ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ፓርኩ ከታለመለት ግብ አንጻር ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነው ማለት አያስችልም፤ ለዚህ ደግሞ ለፓርኩ የታሰበው የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት በወቅቱ አለመጠናቀቅ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶችም ሥራ ለመጀመር በተደጋጋሚ የመብራት ኀይል አቅርቦት አለመኖሩን እንደ ምክንያት ያነሱታል ነው ያሉት፡፡
እስካሁን በቁርጠኝነት ወደ ሥራ ከገቡ ሁለት ኢንዱስትሪዎች በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ 32 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በፓርኩ ያሉ ችግሮችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ፓርኩ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ወደ ሥራ እንዲገባ እና በታለመለት ልክ ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባልም ብለዋል፡፡
የቡሬ ደብረ ማርቆስ ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ገዛኸኝ ካሳሁን የቡሬ ደብረ ማርቆስ የኀይል ሰብስቴሽን ግንባታ በ9 ነጥብ 1 ሄክታር መሬት የሚያርፍ ግንባታ መኾኑን ገልጸዋል።
በቲ ዋን የቻይና ፕሮጀክት የሚገነባው ስብስቴሽኑ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ገደማ ሲጀመር በ18 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎም ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ግንባታው ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የቆየውን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ወደ ሥራ መገባቱንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ግንባታው በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
የመብራት ኀይል መስጫ ሰብስቴሽኑ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ 200 ኪሎ ቮልት የሚኾን ኀይል ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
ይህ የኤልክትሪክ ኀይል ፓርኩ በውስጡ የያዛቸውን ኢንዱስትሪዎች ሙሉ በሙሉ ለማንቀሳቀስ የሚያስችል የኀይል አቅርቦት ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
