
ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ከተማ ጉባኤው ሲካሄድ ታሪካዊ የኾነችው ጣና ነሽ ፪ ከቦታዋ ደርሳ ሥራ በጀመረችበት ወቅት መኾኑ ጉባኤውን ስኬታማ ያደርገዋል ብለዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ብልጽግና ስኬቶች የጀርባ አጥንት ኾኖ ያገለግላል ብለዋል። ዘርፉ የሰው ኀይልን ከሥራ እና ምርትን ከገበያ ጋር በማገናኘት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የኀይል መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። የብዙኀን ትራንስፖርትን ለማስፋፋትም ልዩ ትኩረት ተሠጥቶታል ነው ያሉት።
ለቱሪዝም ምቹ የኾነ የትራንስፖርት አማራጮች ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ አንስተዋል። የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ዓላማው ተቋም መገንባት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ክልሎች የዘርፉን የሰው ኀይል ላይ ትኩረት መሥጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይገባል ነው ያሉት። ክልሎች በቅንጅት፣ በቁጭት እና በእልህ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘውዱ ማለደ የክልሉ መንግሥት አገልግሎቱ እንዲዘምን ለትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉ ሰፊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ከ142 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በዲጂታል ሲስተም ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አመላክተዋል። አምስት ዘመናዊ የትራፊክ ኮምፕሌክስ እንዲሁም 252 መናኸሪያዎችም መኖራቸውን አስታውቀዋል።
133 የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት እና 22 የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። የሰውን ሕይወት የሚቀጥፈው እና ንብረትን የሚያወድመው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኀላፊ ያብባል አዲስ በበኩላቸው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ለአንድ ሀገር የደም ስር ነው ይላሉ። ዘርፉ ለሁሉም ሴክተሮች አስቻይ የኾነ የእድገት መሠረት ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን ሀገራዊ እና አሕጉራዊ ገጽታን መሠረት ያደረጉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተዋል። ትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን ለአፍሪካ ተምሳሌት ለመኾን ታሳቢ በማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በከተማዋ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን በማሥፋት፣ የተሽከርካሪ ተርሚናሎች በመገንባት እና በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
