
ጎንደር: ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኙ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እና የምክር ቤት ምሥረታን አካሂደዋል።
በመድረኩ የፋይናንስ፣ የፍትሕ፣ የፓርቲ እና የሲቪክ ማኅበራት አካላት ተገኝተዋል።
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና ማኅበረሰብን በልማት እና ዴሞክራሲ ግንባታ እንዲያግዙ በሕግ ማዕቀፍ የተቋቋሙ መኾኑን የተናገሩት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ አየልኝ ደሳለኝ ናቸው።
በቀደሙት ዘመናት የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና መንግሥት ተግባብተው ለመሥራት ይተገብሩ እንደነበር ያነሱት አቶ አየልኝ አሁን ላይ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩን ገልጸዋል።
የተሰጣቸውን ነጻነት በመጠቀም ማኅበረሰብን ማገዝ ላይ የማይሠሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩንም አንስተዋል።
የጋራ ምክር ቤት መመሥረቱ ተጠያቂነት እንዲኖር እና በጋራ መሥራት የሚያስችል ነውም ብለዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ50 በላይ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበራት መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ገንዘብ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ማንዴ ዘሜ ናቸው።
የሲቪክ ማኅበራቱ ከአባላት እና ከማኅበረሰቡ በሚሰበስቡት ሃብት የበጎ አድራጎት ሥራን እያከናወኑ ቢገኙም ከፍተኛ የኾነ የፋይናንስ እጥረት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
የዞኑ ገንዘብ መምሪያም ይሁን፤ ሌሎች ተቋማት ለማኅበራቱ እገዛ ሲያደርጉ እንደማይስተዋል ያነሱት ምክትል ኀላፊው የጋራ ምክር ቤቱ መመሥረት እገዛ እንድናደርግ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
መተጋገዝ እና መተባበር ለሲቪክ ማኅበራቱ ቀጣይነት ሚናው የጎላ ስለመኾኑም አንስተዋል።
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ዕድገት መሠረት መኾናቸውን በመድረኩ የጋራ ምክር ቤት መመሥረቱ ሲቪክ ማኅበራቱ ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት እንደሚፈታም የምክክሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ተሳታፊዎቹ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲቪክ ማኅበራት በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙ ቢኾንም በልማት እና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ የኾነ የፋይናንስ እጥረት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሲቪክ ማኅበራት በሁሉም አካባቢ የልማት እና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
