”ሰላምን የምናገኘው ስለተመኘነው ሳይኾን ስንሠራው እና ስንሳተፍበት ነው” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

3

ባሕር ዳር: ኅዳር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር 20ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን ከከተማው ነዋሪዎች እና ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በውይይት እያከበረ ነው።

”ለዴሞክራሲያዊ መግባባት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት በውይይቱ በተከበረው በዓል የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤ ጌትነት ዕውነቱ (ዶ.ር) እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት የኢትዮጵያ ብዝኅ ማንነት ጌጥ ነው። ሀገሪቱ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የኾነችውም አባቶች ብዝኀነቷን ለትብብር ስለተጠቀሙበት ነው ብለዋል።

የብሔር ብሔረረቦች ቀን የሚከበረው ብዝኀ ማንነት ስላለ ነው ያሉት አቶ ጎሹ በሁሉም ነገሮች ላይ በአንድነት ለመቆም የበዓሉ መከበር ጠቀሜታው ከፍ ያለ እንደኾነ ጠቁመዋል።

በዓሉ ኢትዮጵያዊነትን እና አንድነትን መሠረት አድርጎ እየተከበረ መኾኑን የጠቆሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የ’በዳይ ተበዳይ’ ትርክትን አስቀርቶ አንድነትን ለማጠናከርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብም በዓሉን ሲያከብር ጥያቄዎቹን ሁሉ በሰላም ለመፍታት የሚወያይበት መኾን እንዳለበትም አንስተዋል። በሰላም እጦት የተከፈለው ዋጋ እንዳይደገም መመካከር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በዓሉ የሚከበረው ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተባብረው የገነቡት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ በተመረቀበት ማግሥት መኾኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተባብረው ኢትዮጵያን በመጠበቅ ለዛሬው ሁኔታ ማድረሳቸውንም አንስተዋል። አሁንም በመከባበር እና በመወያየት ሰላማዊ፣ ለዜጎቿ ምቹ እና የለማች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ብዝኀነትን በተግባር ያስተናገደ መኾኑን የጠቀሱት ዋና አፈ ጉባኤዋ በሀገር ደረጃም የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዕውቅና የተሰጠበት ሀገር ነው ብለዋል። ለዚህም ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ በንቃት እና በትብብር የመሥራታቸውን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።

አሁን እያጋጠመ ያለውን የአንድነት መላላት ለመፍታት በዕውቀት እና ዕውነት ላይ ተመስርቶ በመነጋገር መፍትሄ የማበጀትን ጠቀሜታም አንስተዋል። ኅብረ ብሔራዊነት የውበት እና የአንድነት ማጠናከሪያ እንጂ ልዩነት መፈለጊያ እንዳልኾነም ጠቁመዋል።

በክልሉ ያጋጠመውን ግጭትም በውይይት ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። “ሰላምን የምናገኘው ስለተመኘነው ሳይኾን ስንሠራው እና ስንሳተፍበት ነው፤ ለሰላም የኔ ድርሻ ምንድን ነው ብለን እናስብ” ብለዋል።

በበዓሉ አከባበር በሕገ መንግሥት እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጽንሰ ሃሳቦች እና ሀገራዊ ኹኔታዎች ላይ መወያያ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ነው።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የታቀዱት የልማት ዕቅዶች ለስኬት እንዲበቁ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፉ ወሳኝ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleኅብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ኢትዮጵያን ማበልጸግ ይገባል።